በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ በህብረተሰብ ጤና የሶስተኛ ድግሪ የትምህርት ፕሮግራም በመክፈት እያስተማረ ሲሆን በነሐሴ18/2013 ዓ.ም የመጀመሪያውን ተመራቂ የ3ኛ ድግሪ መመረቂያ የማሟያ ጥናት ውጤትን በውስጥ እና በውጪ ገምጋሚ ኮሚቴዎች አስገምግሟል፡፡
ዶ/ር መሳይ ሀይሉ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት በዕለቱ እንደተናገሩት ኮሌጁ ከዚህ በፊት በውጪ ሀገር ከሚገኘው በርገን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሶስተኛ ድግሪ ፕሮግራሞችን ያስተምር የነበር ሲሆን የአሁኑ ግን የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት በማስተማርና በምርምር በቂ እውቀትና ልምድ ካላቸው ተቋማት በመቀመር የራሱን የትምህርት ስርዓት አዘጋጅቶ ፕሮግራሙን በመክፈት የመጀመሪውን ተማሪ የጥናት ውጤት እንዳስገመገመ እና ተመራቂውም የተሰጡትን አስተያየቶችና ማስተካከያዎችን በማረም የጥናቱ ውጤት ለምረቃ እንደሚበቃውም ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር መሳይ አክለውም ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይልን ለማፍራት የድህረ-ምረቃ ስርዓተ ትምህርትን በመቅረጽ ፕሮግራሞችን ለመክፈት መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እና ከመደበኛ በጀት በተጨማሪም የተለያዩ የትብብር ፕሮጀክቶችን በማቀናጀት በርካታ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
እጩ ተመራቂ ሀብታሙ በየነ ጥናታቸውን “በጽኑ የታመሙ ጨቅላ ህጻናቶች የቅብብሎሽ(ሪፈራል) አገልግሎቶችና ተግዳሮቶቻቸው“ ላይ እንደሰሩ በመግለጽ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህጻናቶች ወደተገቢው የጤና ተቋማት እንደማይላኩ፣ የጤና ባለሙያዎች የቅብብሎሽ ስርዓቱን በመመሪያው መሰረት እንደማይተገብሩ፣ የህጻናቱ ወላጆችም ወደተላኩበት የጤና ተቋማት ልጆቻቸውን በአግባቡ እንደማልኩ እና በተያያዥነትም የክህሎትና እውቀት ክፍተት፣ የልየታ ችግሮች፣ የኢኮኖሚ አቅም ዝቅተኛ መሆን እና የቦታ ርቀት በጥናቱ የተገኙ ውጤቶች መሆናቸውን ገልጸው ለእነዚህንም ተግዳሮቶች ለመፍታት ይረዳ ዘንድ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች እና ለጤና አግልግሎት ባለሙያዎች የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦች በጥናቱ ላይ መካተታቸውን ተናግረዋል፡፡