የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ለመጀመሪያ ድግሪ አዲስ ገቢ መደበኛ ተማሪዎች ስልጠና ሰጠ

ከነሐሴ 15 እስከ 16 ቀን 2013 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት በአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት  በዩኒቨርሲቲው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ስልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡

በዚሁ ስልጠና ላይ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘለቀ ኤርፍጮ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን ስልጠናው የተዘጋጀበትን ዓላማ ባብራሩበት ወቅት እንደገለጹት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሁሉም የተፈጥሮ እና ማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች የትምህርት ክፍሎቻቸውን ከመምረጣቸው በፊት በጋራ ሆነው የፍሬሽ ማን ኮርስ እንዲወስዱ በመደረጉ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ይዞ በማስተማር ላይ እንደሚገኝና በባለፈው ዓመት ዩኒቨርሲቲውን ፍሬሽ ተማሪዎች ሆነው ከተቀላቀሉ መካከል ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው በመሰናበታቸው ይህን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንዴት መቆየት እንዳለባቸው ለማስገንዘብ ስልጠናው ተዘጋጅቷል ብለዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም ስልጠናው ሁለት ርዕሶች ያሉት እና የመጀመሪያው Study Skills ወይም የአጠናን ዘዴዎች የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ Secrets of Success in Examination ወይም በፈተና ስኬታማ የመሆን ምስጢር መሆኑን እና አሰልጣኞችም በመስኩ ብዙ ጥናትና ምርምሮችን ያካሄዱና ልምድ ያላቸው መምህራን መሆናቸውን ገልጸዋል።

በማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የኢንግሊዝኛ ቋንቋ እና ስነ-ጽሁፍ መምህር  እንዲሁም የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበበ ጥላሁን(ረዳት ፕሮፌሰር) በበኩላቸው ስልጠናው በባለፈው ዓመት የነበረውን የአዳዲስ ተማሪዎች የመባረር ምጣኔን ለመቀነስ እንዲሁም የመዝለቅ ምጣኔን ለመጨመር በማሰብ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን ተናግረዋል። አቶ አበበ ጥላሁን አክለው እንደገለጹት ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ስልጠና ላይ ከ4800 በላይ ተማሪዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ እና ከስልጠናው መጠናቀቅ በኋላ በተማሪዎች ውጤት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ይኖራል ብለው እንደሚያስቡ የገለጹ ሲሆን ማስተባበሪያ ጽ/ቤታቸው ከተማሪ ተወካዮች ጋር በመሆን ተማሪዎች በቂ ትምህርት እያገኙ መሆናቸውን፣ ቤተ መጽሀፍቶች በቂ አቅርቦት መያዛቸውን እንዲሁም ቤተ- ሙከራዎች በበቂ ግብዓቶች መደራጀታቸውን እንደሚከታተል እና ይህ ሁሉ የተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የመዝለቅ ምጣኔን ለመጨመር እና የተሻሉ ተማሪዎች ሆነው ህዝብ እና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ለማስቻል መሆኑን አስረድተዋል።

በመጨረሻም በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ዘለቀ ሲናገሩ አብዛኛው የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ በሚቀላቀልበት ወቅት ቀደም ሲል ከነበረበት የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከባቢ የተለየ ስለሚሆንበት ግራ እንደሚጋባ እና ይህም ለስነ-ልቦናዊ ጫና ስለሚዳርገው በውጤቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ገልጸዋል። ስለዚህም እንዲህ ዓይነቱ ስልጠና መዘጋጀቱ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ወቅት ምን አይነት የአጠናን ዘዴን ቢጠቀሙ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉና በፈተና ወቅትም እንዴት በስነ ልቦናውም ይሁን በእውቀት እራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ክህሎት እንዲጨብጡ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et