ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩ ከየዲፖርትመንቱና ከተለያዩ የትምህርት ክፍሎች አብላጫ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል፡፡
በወቅቱ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ደሳለኝ ግርማ በመክፈቻ ንግግራቸው ይህ ፕሮግራም የተማሪዎችን የእስካሁን አፈፃፀም መሠረት በማድረግ ከየትምህርት ክፍሉ ከፍተኛ አጠቃላይ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ በንግግራቸው ይህ ፕሮግራም የተማሪዎችን የእስካሁን አፈፃፀም መሠረት በማድረግ ከየትምህርት ክፍሉ ከፍተኛ አጠቃላይ ውጤት ወይም CGPA ላስመዘገቡ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም የዚህ አይነቱ ማበረታቻዎች የበረታው ተማሪ እንዲቀጥልበት፤ ለሌሎች ደግሞ ተግተው ይሰሩ ዘንድ ማነቃቂያ እንዲሆን ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የላብራቶሪዎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የፕሮግራሙ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ምህረቱ ገብሬ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ አምስት ፋካሊቲዎች፣ ሀያ የትምህርት ፕሮግራሞች እና አስራ ዘጠኝ የትምህርት ክፍሎች ያሉት መሆኑን ጠቁመው፤ የዛሬው የማበረታቻ ሽልማት በእነዚህ የትምህርት ክፍሎች ከሚማሩ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ አመት ተመራቂ ተማሪዎች መካከል የዚህኛውን መንፈቀ አመት ውጤት ሳይጨምር የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ተማሪዎች የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፋሲካ ቤቴ ሲናገሩም መሰል የማበረታቻ እና ልዩ እውቅናን የሚሰጡ ፕሮግራሞች በብዛት ሊካሄዱ እንደሚገባና ከዚህም በላይ ሰፍቶ መምህራንን እና የአስተዳደር ሰራተኞችን ጭምር አቅፎ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። አክለውም ጥሩ ውጤት ስለተፈለገ ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ትኩረት ሰጥቶ መስራት፣ መስዋዕትነት መክፈል፣ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እና ለዚህም በእምነት እና በዓላማ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። ተማሪዎች ላስመዘገቡት የላቀ ውጤት ማበረታቻ መስጠት የተሻለ የትምህርት ፍላጎትን የሚፈጥር ይህም ደግሞ መምህራን ለተማሪዎቻቸው የተሻለ እውቀትን እንዲያስጨብጡ የሞራል ስንቅ ይሆናል ብለዋል።
በመጨረሻም የተለያዩ መምህራን ተሞክሮዎቻቸውን ያካፈሉ ሲሆን ለተማሪዎችም ባስተላለፉት መልዕክት የዛሬ ተሸላሚዎች እንዲሁም ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ብዙ ነገር መስራት የምትችሉበትን የወጣትነት አቅማችሁን በእውቀት በማበልጸግ ለሀገራችሁ ብዙ ማበርከት ይጠበቅባችኋል ብለዋል። በዕለቱ ፕሮግራም ላይ የኢንስቲትዩቱን ዳይሬክተር ጨምሮ የየትምህርት ክፍሉ ኃላፊዎች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።