በሆስፒታሉ የአስተዳደር ልማት ዳይሬክቴር አቶ ኡርጌሳ ዋርሳሞ ነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው በዚሁ ፕሮግራም ማጠቃላያ ላይ እንዳስታወቁት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከግብ ለማድረስ የሆስፒታሉ ሰራተኞች በራሳቸው ተነሳሽነት ባደረጉት እንቅስቃሴ በ2 ሰዓታት ውስጥ ከ3 ሺ በላይ ሀገር በቀል ዛፍ ችግኖች መትከላቸውን አስታውቀዋል፡፡
የችግኝ ተከላው ፕሮግራም የተካሄደው በ2 ሄክታር መሬት ላይ በዩኒቨርሲቲው ስር ተቋቁሞ ባለፈው ዓመት ለአገልግሎት ለበቃው የካንሰር ማዕክል ዙሪያ መሆኑንና የተራቆቱ ስፍራዎችን በደን ከማልበስ ባሻገር ታማሚዎች ንጹህ አየር እንዲያገኙ ታስቦ እንደሆነ አቶ ኡርጌሳ አስገንዝበዋል፡፡ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የችግኝ አቅርቦት ወጭውን የሸፈነ ሲሆን በቀጣይም ለምግብነት የሚያገለግሉ ፍራፍሬዎችን ለመትከል በዕቅድ መያዙን ገልፀው ስራተኞች ላሳዩት በጎ ተነሳሽነት አመስግነዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ከ200 በላይ የሚሆኑ የሆስፒታሉ ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን አንዳንዶቹ በዚሁ ጊዜ በሰጡት አስተያየት ችግኞችን ተክሎ መንከባከብ የመሬት መሸርሸርን ከመቀነስ ባሻገር ንጹህ አየር በማግኘት ለህብረተሰብ ጤና ወሳኝ መሆኑንና ከሙያቸውም አንጻር ለአከባቢው ነዋሪዎች ምሳሌ ለመሆን በፕሮግራሙ መሳተፋቸውን አስረድተዋል፡፡