ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ተፋሰስ ልማት ባለስልጣን መስሪያ ቤት ጋር በሀዋሳና ዝዋይ ስምጥ ሸለቆ ጉዳዮች ላይ በሚሰራው ፕሮጀክት ዙሪያ ምክክር አደረገ

ሐምሌ 19 2013 ዓ.ም በሀዋሳ ገዛሄኝ እና እልፍነሽ ሪዞርት ሆቴል ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ተፋሰስ ልማት ባለስልጣን ጋር በመተባበር በሚሰራው የምርምር ፕሮጀክት ጅምር አውደጥናት በማስመልከት የምክክር መድረክ  አዘጋጅቷል፡፡

በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የኦሮሚያ፣ የሲዳማ እና የደ/ብ/ብ/ህ ክልሎች እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ደን ልማት ባለስልጣን ተወካዮች፣ የስምጥ  ሸለቆ ሀይቆች ተፉሰስ ልማት ባለስልጣን  ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድን አባላት፣ ተጋባዥ  ባለሙያዎች እና  ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ንግግር ሲያደርጉ በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ አከባቢያዊና ስነ-ምህዳሪያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሀይቆች በህዝብ ብዛት መጨመርና በአየር ለውጥ ምክንያት በሚከሰተው ተፅዕኖ ለብክነትና ለጥፋት እየተዳረጉ መሆናቸውን በመገንዘብ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለተፋሰሱ ልዩ ትኩረት ሰቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ፕሬዝዳንቱ በመቀጠልም ዩኒቨርሲቲው የተፋሰስ ልማት ባለስልጣን መስራያ ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በትብብር መጠነ ሰፊ የምርምርና የማህበረሰብ ልማት ስራዎችን አብሮ እየሰራ መቆየቱን ጠቅሰው የተፋሰስ ልማት ባለስልጣን መ/ቤት ሀላፊዎች እና ባለሙያዎች የፕሮጀክቱን የድርጊት መርሀ ግብር አንድ ላይ ገምግመው የሚያስጀምሩበት የመጀመሪያ ፕሮግራም ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል ።

ዶ/ር አያኖ ባራሶ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ እንደገለጹት በዚህ አውደጥናት ከኢትዮጵያ ተፋሰስ ልማት ባለስልጣን መስራያ ቤት ጋር በትብብር ልንሰራ ያቀድናቸውን ሁለት የምርምር ፕሮጀክቶች ጅምር ሪፖርት እና የተግባር መርሀ-ግብር በመስማትና በመወያየት በጋራ መረዳት ላይ የሚደረስበት መሆኑን እንዲሁም የተፋሰስ ልማት መ/ቤት ላለፉት አምስት አመታት በሀዋሳ ሐይቆች እና በዝዋይ-ሻላ ተፋሰሶች ላይ የሰራቸው  የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ያስከተሉትን ተፅዕኖዎች በማጥናትና የተሰሩ ሥራዎችን ውጤታማነት በመገምገም  የወደፊት የልማት ስልት የሚቀይስ  ይሆናል ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ተፋሰስ ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አዳነች ያሬድ በበኩላቸው ባለስልጣኑ ወተር ሼዴ ወይም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል አፈር እንዳይሸረሸር የውሀ መጠንና ጥራት ላይ ትኩረት እያደረገ መቆየቱን ገልፀው እስካሁን በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ውጤቶችን ለሌሎች አከባቢዎች ለማስተላለፍና የታዩ ክፍተቶች ደግሞ መንስኤዋቻቸውን በመለየት እንዳይደገሙ ለመስራት የተካሄደ የውይይት መድረክ አካል ነው ያሉት ዳይራተሯ እስካሁን በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ለህብረተሰቡና በሀገር ደረጃ የተገኘው ጥቅም ምን እንደሚመስል አስረድተው የተሰሩ ፕሮጀክቶችን ሀላፊነት ለሚሰማው አካል ለማስተላለፍ እንደሚሰራም ጠቁመዋል። ከዚህ በፊት ረዥም ጊዜ ይወስድ የነበረው የተፋሰስ ልማት ስራ ፕሮጀክት አሁን ላይ በአጭር ጊዜ እንዲያልቅ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንና  ህብረተሰቡን የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

በመጨረሻም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይራክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ባዩ ቡንኩራ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሀገር በቀልና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት በርካታ ስራ እየሰራ እንዳለ ገልፀው ከእነዚህ ስራዎች አንዱ ከኢትዮጵያ ተፋሰስ ልማት ባለስልጣን ጋር በመሆን በሀዋሳና በዝዋይ ስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ የሚሰራ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ የውይይት መድረክም  በፕሮጀክቱ ዙሪያ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድን አባላት ሲያካሂዱ የቆዩትን ጥናታዊ ጽሑፍ  ሪፖርት አቅርበው  ከባለድርሻ አካላት ጋር  የተደረገበት  የውይይት መድረክ በመሆኑ ለወደፊት የተቀናጀ ስራ በመስራት ውጤታማ ለመሆን በሚደረገው ጉዞ ውስጥ የምክክሩ ውጤት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት እምነታቸውን ገልጸዋል ።

                                                                                                           

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et