ሰኔ 11 ቀን 2013 ዓ.ም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማና የ2014 ዕቅድ ዝግጅት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል፡፡
ዶ/ር ደብረወርቅ ደበበ የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ዲን እንደተናገሩት የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከመከርን በኃላ ለቀጣዩ ዓመት ግብዓቶችን በመውሰድ የቀጣዩን ዓመት ዕቅድ የበሰለ፣ተጨባጫ መረጃዎችን የያዘና ሊተገበር የሚችል ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ፕሮግራም ሲሆን ከኮሮና ጋር በተያያዘ የ2012 ዓ.ም የትምህርት አሰጣጥ ስርዓቱ በመስተጓጎሉ ምክንያት በተማሪዎቻችን፣ በመምህራኖቻችን፣ በአስተዳደር ሰራተኞቻችን እና በፋይናንስ ሰርጫቱም ላይ ተደራራቢ ጫና በመፈጠሩ፣ ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ላይ በመሆናችን ይሄንን ምርጫ አስመልክቶ መምህራኖቻችን ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተጨማሪ ተደራራቢ ስራዎች በመዳረጋቸው እና ከግዢ ስርዓቱ ጋር በተያያዘ የገበያ አለመረጋጋት በመኖሩ የግብዓቶች መዘግየትና የጨረታ መሰረዞች የገጠሙን ተግዳሮቶች ቢሆኑም በተቻለ መጠን በመቀናጀትና በመናበብ ስንሰራ ቆይተናል ብለዋል፡፡
የኮሌጁ የአካዳሚክ ጉዳዮች ተባባሪ ዲን አቶ አስፋው ዘውዴ እንደገለጹት ኮቪድ-19 ወረርሽኝን እየተከላከልን የመማር ማስተማሩን ስርዓት ለማስቀጠል የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ፣ የአሰራርና የመልካም አስተዳደር ስርዓቶችን በማዘመን፣ በየግዜው መረጃዎችን በማየትና በመተንተን እና ከአጋር ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ አብሮ በመስራት የቀጣዩን ዓመት ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እንደታሰበ ገልጸዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ በቀረበው ሪፖርት መሰረት የኮሌጁ የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም 77% በመሆኑ መካከለኛ ደረጃ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ እና በቀጣዩ ዓመትም አንድ የሶስተኛ ድግሪ በPhilosophy of Doctor in Law and Governance ለመክፈት ስርዓተ ትምህርት እየተቀረጸ መሆኑ ታውቋል፡፡