ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰቡ ችግር በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ተደራሽነቱን በማስፋት የተለያዩ መርሀ ግብሮችን በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ተደራሽ ካደረጋቸው መካከል በሲዳማ ክልል ወንሾ ወረዳ ባዘጋጀው መርሀ ግብር ላይ የተገኙት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ፍሬው ካሳ በንግግራቸው እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፉ የማህበረሰቡ ችግሮች በሆኑ በርካታ ጉዳዮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እና የቁሳቁስ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም የዛሬው መርሀ ግብር በወንሾ ወረዳ የማህበረሰቡ ችግር ሆኖ በተገኘውን የሙጃሌ በሽታ ዙሪያ በቂ ግንዛቤን ለመፍጠር የዩኒቨርሲቲው ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከወረዳው የጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት መሆኑን ገልጸው መሰል የማህበረሰቡ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት እና መፍትሄዎችን በማፍለቅ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል ።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ፍሰሀ ቦንጃ በበኩላቸው ይህ የሙጃሌ በሽታ በመንግስት ደረጃ እንኳን በቂ ትኩረት ስለተነፈገው በአሁኑ ወቅት በህብረተሰቡ ላይ የጤና፣ የማህበራዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጉዳቶችን ማስከተሉን ተናግረው ቀደም ሲል በስምንት ቀበሌዎች ላይ በተካሄደ ጥናት ከሰባ በመቶ በላይ የማህበረሰቡ ክፍሎች የበሽታው ተጠቂ ሆነው መገኘታቸውን ተከትሎ በተወሰደው የመከላከል ስራ ውጤት በመገኘቱ የዛሬው የግንዛቤ ማስጨበጫም የበሽታውን ደረጃ በመግታቱ ረገድ ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። ኃላፊው በማጠቃለያቸውም መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የመከላከል ስራዎች በሌሎች ችግሩ በሚታይባቸው የክልሉ አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ሰለሞን አስናቀ የሙጀሌ ቁንጫ በመጠኗ በጣም ትንሽ እና በአብዛኛው ጊዜ ቆሻሻ እና አቧራማ በሆኑ አከባቢዎች እንደምትገኝ ገልጸው አብዛኛውን ጊዜ ይህ በሽታ የግል ንፅህናን ባለመጠበቅ እና ቆሻሻማ በሆኑ አካባቢዎች በሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ እንደሚስተዋል ተናግረዋል። ዶክተሩ አክለው እንደተናገሩት በበሽታው ተጠቂ የሚሆኑ ሰዎች ከሚደርስባቸው የጤና እክል በተጓዳኝ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን ለመፈፀም እክል እንደሚገጥማቸው እና የስነ-ልቦና ጫና ይደርስባቸዋል ብለዋል። በሽታው በአብዛኛው ከድህነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ንፅህናን በመጠበቅ፣ የሙጀሌ ቁንጫ በሚገኝበት አካባቢ የኬሚካል ርጭት በማካሄድ እና ቆሻሻዎችን በአግባቡ በማስወገድ በሽታውን መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመጨረሻም የወንሾ ወረዳ ጤና ቢሮ ኃላፊው አቶ ታምሩ ሻላሞ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተጣለበትን ማህበረሰቡን የማገልገል ኃላፊነት ለመወጣት እያከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚያደንቁ እና የወረዳው ማህበረሰብ ችግር በሆነው በሙጀሌ በሽታ ላይ ለማህበረሰቡ ላዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብር በወረዳው ህብረተሰብ እና በጤና ቢሮው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ኃላፊው አክለውም ከዩኒቨርስቲው ጋር በጋራ የሚሰራው ስራ በዚህ እንደማያበቃና በቀጣይነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸውን ገልጸዋል።