የኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት በተሻሻለ የእንጨት ምድጃ አሰራር መሰረታዊ የዲዛይን መመሪያና የጋዝ ፋየር ምድጃ አጠቃቀም ላይ ስልጠና ሰጠ

ሰኔ 8 ቀን 2013 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ አዳራሽ በተካሄደው በዚሁ ስልጠና ወቅት የተገኙት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ መጠን በተለያዩ ዘርፎች ላይ በሚደረጉ ምርምሮች እና አዳዲስ ፈጠራዎችን ለማሳደግ በሚሰሩ ስራዎች ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ዶክተሩ አክለውም በዛሬው እለት የቀረበው ወጪ ቆጣቢ እና ውጤታማ የሆነ ምድጃ ከሀሳቡ መነሻ እስከ ትግበራው ድረስ በትብብር ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው ፈጠራው መብራት ባልገባባቸው የሀገራችን ክፍሎች በጪስ ምክንያት ይከሰቱ ከነበሩ የጤና እክሎች እንዲሁም አላግባብ የሚፈፀሙ የደን ጭፍጨፋዎችን ተከትሎ በስርዓተ-ምህዳሩ ላይ የሚፈጠረውን አሉታዊ ተጽዕኖ በእጅጉ ይቀንሳል ብለዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ስር የሚገኘው የቴክኖሎጂ ሽግግርና ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ ዶ/ር ባዩ ቡንኩራ በበኩላቸው ዳይሬክቶሬ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ለማዘመን በበርካታ ዘርፎች ላይ ስራን እየሰራ እንደሚገኝ እና በዚህም ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው አብዛኛው የሀገሪቱ ህዝብ ለዕለት ተዕለት ማብሰያነት የማገዶ እንጨት ተጠቃሚ በመሆኑ በዚሁ ዘርፍ የሚካሄዱ ፈጠራዎች በቀጥታ እና በአፋጣኝ የማህበረሰቡን ችግሮች የመፍታት አቅም አላቸው ብለዋል። ዳይሬክተሩ በንግግራቸው በዚሁ ዘርፍ ለተሰማሩ ማህበራት የሚሰጠው ስልጠና ምርቱ በብዙ ቦታዎች ላይ መሰራት እንዲችል እንዲሁም ተደራሽነቱ እና የተጠቃሚው ቁጥር ብዙ እንዲሆን ስለሚያደርግ ስልጠናውን በቀጣይነትም ለሌሎች በሙያው ለተሰማሩ ማህበራት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው እና መስሪያ ቤታቸው ይህ ምርት በቂ የገበያ ተደራሽነትን ያገኝ ዘንድም የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግረዋል።

የቴክኖሎጂ ሽግግርና ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር አስተባባሪ ረ/ፕሮፌሰር ስመኝ ሰርካ ሲናገሩ ጋዝ ፋየር ምድጃን ሰልጣኞች ቀደም ሲል በእጃቸው ከሚገኙ የምድጃ አማራጮች ጋር በማነፃፀር በተጨማሪነት የተገኘውን አዲስ ፈጠራ ምንነት ይገነዘቡ ዘንድ ስልጠናው አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። ይህ አዲስ ፈጠራ በጥራቱ እንዲሁም  በማገዶ ቆጣቢነቱ የተሻለ በመሆኑ በሰልጣኞች በእጅጉ ተመራጭ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

በዕለቱ ስልጠናውን የሰጡት እና ከፈጠራ ግኝቱ ፈጣሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ መምህር እና ተመራማሪው ዶ/ር ሽመልስ ንጋቱ የስልጠናውን አስፈላጊነትን በገለጹበት ወቅት ለተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት ሰልጣኞች ዛሬ የሚያገኙትን አዲስ ዕውቀት ከቀደመ ልምዳቸው ጋር በማገናኘት በቀጣይነት የተሻሉ የምድጃ አማራጮችን እንዲያቀርቡ ተናግረዋል። ተሳታፊዎች ምርቱን ለገበያ ይዘው በሚወጡበት ወቅት እና ለተጠቃሚዎች በሚያቀርቡበት ጊዜ በቂ ስለ ምርቱ የተካፈሉትን ዕውቀት በአግባቡ ይተላለፉ ዘንድ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et