ከሰኔ 3-5 ቀን 2013 ዓ.ም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየካሄደ ያለው ስልጠና አዲሱን የዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ስር የሚገኘው የዲሲፕሊን ጉዳዮች አስተዳደር ቡድን ከተማሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ላላቸው የአስተዳደር ሰራተኞች ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሲሆን የዳይሬክተሩ ጽ/ቤት ሰራተኞችን ጨምሮ የተማሪዎች ምግብ አገልግሎት ቡድን፣ የተማሪዎች መኝታ አገልግሎት ቡድን፣ የተማሪዎች ጤና አገልግሎት ቡድን፣ የተማሪዎች ጋይዳንስና ካውንስሊንግ፣ የአካል ጉዳተኞች ማስተባበሪያ ማዕከል እና የግቢው ፖሊስና ደህንነት ጽህፈት ቤት ተሳታፊዎች ሆነዋል።
በቦታው ተገኝተው ስልጠናውን የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ከበደ በቃለ ምልልሱ ወቅት እንደተናገሩት ቀደም ሲል በ2006 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው አዘጋጅነት በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የተማሪዎች ስነ ምግባር መመሪያ ተዘጋጅቶ በስራ ላይ ሲውል የነበረ መሆኑን ገልጸው በትግበራው ወቅት ክፍተቶች ይስተዋሉ እንደነበር ተናግረዋል። ነገር ግን ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተላከውንና በሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር የተዘጋጀውን አዲሱን የተማሪዎች ዲሲፕሊን መመሪያ ተቀብሎ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም በዚህ ዙር የሚሰጠው ስልጠና ወቅቱ የአዳዲስ ተማሪዎች ቅበላ የሚደረግበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እኚህን ተማሪዎችን ዘወትር በቅርበት ለሚያገኙ ሰራተኞች እየተሰጠ እንደሚገኝ እና በስልጠናው የሚሳተፉት አካላት ተማሪዎች የመጡበትን የመማር ዓላማ በስኬት ተወጥተው ቤተሰብና ሀገር የጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዲችሉ ከተለመደው ተማሪዎችን በተደጋጋሚ ከመቅጣት አሰራር በመውጣት አስተማሪ በሆኑ ቅጣቶች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የዲሲፕሊን ጉዳዮች ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ማቴዎስ ማኖሬ በበኩላቸው ምንም እንኳን መመሪያው የተማሪዎች የዲሲፕሊን መመሪያ ተብሎ ቢጠራም አንድ አንድ ጊዜ በአስተዳደር ሰራተኞች በኩልም የስነ ምግባር ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል። ስልጠናውን የሚሳተፉ አካላት ይህንን ክፍተት በማረም ተማሪዎችን በቤተሰባዊነት በመንከባከብ የመማር ማስተማሩ ሂደት ውጤታማ ይሆን ዘንድ ዓይነተኛ ሚናን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል። በቀጣይም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው አዳዲስ ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚገቡ ተማሪዎችም እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ የተማሪዎች ምግብ አገልግሎት ቡድን መሪው አቶ ስንታየሁ ኃይሉ ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመድበው የሚመጡት አዳዲስ ተማሪዎች ከተለያየ ማህበረሰብና ከተለያየ ባህል ስለሚመጡ በግቢው ውስጥ ያለው አሰራር እንግዳ ሊሆንባቸው ይችላል ብለዋል። በግቢው ውስጥ ሰባት ያህል የምግብ አገልግሎት የሚሰጡ ካፍቴሪያዎች መኖሩንና ከዚህም ውስጥ አንዱ ካፍቴሪያ ተለይቶ ለሙስሊም ተማሪዎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል። የቡድን መሪው አክለውም በዛሬው ስልጠና ባገኙት ግንዛቤ መሰረት ተማሪዎችን በአግባቡ በማስተናገድ ጥፋቶች ሲከሰቱም በማረም የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።