የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲና ምርምር ተቋም ግንቦት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ቤተ-መጽሐፍቱን ባስመረቀበት ወቅት እንደተገለጸው የሀዋሣ ዩኒቨርሲቲን የምርምርና ልህቀት ማዕከልነት ራዕይ ለማገዝ ከ6 መቶ በላይ የምርምርና ቴክኖሎጂ ስራን የሚያግዙ የመጻህፍት ስጦታ ከዶ/ር ሎጋን ኮክራን ለዩኒቨርሲቲው ተበርክቷል።
ለካናዳዊው የሀዋሣ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ሎጋን ኮክራን በተዘጋጀው የምስጋና መርሃ ግብር ቤተ-መጽሐፍቱም የተመረቀ ሲሆን በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የሀዋሣ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዮስ በካናዳዊው የሀዋሣ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ሎጋን ኮክራን ለዩኒቨርሲቲው የተበረከቱት መጻህፍት በበይነመረብ ላይ የማይገኙና ለ3ኛ ድግሪ ተማሪዎች ለምርምርና ጥናታዊ ጽሑፎች አጋዥ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከልነት ራዕይ ሰንቆ በምርምርና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለሚያከናውናቸው ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች መጻህፍቱ ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳላቸው የተናገሩት በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሰሃ ጌታቸው በተበረከተው የመጻህፍት ስጦታ የተከፈተውን አነስተኛ ቤተ-መጽሐፍት የ3ኛ ድግሪ ተማሪዎች በሚገባ ሊጠቀሙ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዶ/ር ሎጋን ኮክራምም በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲውን የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን ለማገዝና የተቋሙን የልህቀት ማዕከልነት ራዕይ ከግብ ለማገዝ መጻህፍቶቹን በተለያዩ ጊዜያት ከካናዳ ማምጣታቸውን ጠቁመው መጻህፍቱ በቁጥር ከ6 መቶ በላይ መሆናቸውንና አጠቃላይ ዋጋቸውም ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በመጨረሻም ዶ/ር ሎጋን ኮክራም ለሀዋሣ ዩኒቨርሲቲ ላበረከቱት ስጦታ ምክትል ፕሬዝዳንቶቹ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን የምስክር ወረቀትም አበርክተውላቸዋል።