ስልጠናው የሚያተኩረው የመረጃ፣ ዕቅድና ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ላይ ሲሆን ኮሌጁ ስልጠናውን ያዘጋጀው ከዕቅድና ተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ጋር በመሆን እንደሆነ ተገልጾአል፡፡
ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም በተዘጋጀው ስልጠና ላይ የማህበራዊ ሳይንስና ስነስብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዳኜ ሽብሩ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የተዘጋጀው ዕቅድ ለመረዳት ከአሁን በፊቱ የተሻለ በመሆኑ በኮሌጁም ሆነ በየትምህርት ክፍሎቹ ደረጃ በደንብ ታቅዶ መሠራት እንዳለበት በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መረጃ አያያዛችንንና ፋይል አደረጃጀታችንን በማዘመን የተቀላጠፈ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ያቀድነውን ስንተግብር እና በአግባቡ ያደራጀነውን መረጃ በጊዜና በጥራት ለማሰራጨት እና ሪፖርት ለማቅረብ ንቁ መሆንና ስልቱን መረዳት ይገባናል ሲሉ ለተሳታፊዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሲያጠቃልሉም ከላይ የተገለጹ ጉዳዮችን ከግምት በማስገባት ይህን ስልጠና እስከሚጠናቀቅበት ሰዓት ድረስ በትኩረት መከታተል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በዕለቱ በዕቅድ ዝግጅትና ሪፖርት አቀራረብ እንዲሁም መረጃ አያያዝ ላይ አቶ ሙሉጌታ ቡርቃ ስልጠናውን የሰጡ ሲሆን በዕቅድ መመራት ውጤታማ ከማድረጉም በላይ ንቁና ብቁ ዜጋ አድርጎ በመቅረጽ አወንታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በመግቢያቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡ ለጥቀውም የዩንቨርሲቲ አቀፍ ግቦችን መነሻ በማድረግ ዕቅድ አዘገጃጀቱን፣ መረጃ አያያዙን እና ሪፖርት አቀራረቡን ሰፊ ትንተና በታከለበት አገላለጽ ለተሳታፊዎቹ አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም በተደረገው ውይይት የመወያያ ጥያቄዎችን በመያዝ አሳታፊ የነበረው ስልጠና እንዳነቃቃቸውና አርያነት ያለውን አገልግሎት ለመስጠት አቅም የፈጠረላቸው መሆኑን ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶች በሰጡት አስተያየት ለማወቅ ተችሏል፡፡