ተቋሙ ግንቦት 27 ቀን 2013 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ባካሄደው በምክክር አውደ ጥናት ላይ በርካታ ታዳሚዎች ተገኝተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ ባራሶ ከሲዳማ ክልል፣ ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር እና ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለተውጣጡ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ዕዉቀቶች የታደለች ብትሆንም ይህን እውቀት በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ከፍተኛ ክፍተት እንደነበር ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት እኚህን ውድ የሆኑ የሀገር በቀል ዕውቀቶችን በሳይንሳዊ ምርምሮች በመደገፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ እንደሚገኝ እና በዚሁ ረገድ ዩኒቨርስቲው ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ምርምሮችን ሲያካሂድ መቆየቱን አብራርተዋል። እስከ አሁን ባለው ሂደትም በአቅራቢያው በሚገኘው የሲዳማ ክልል ትኩረቱን በማድረግ ጥናቶችን ማካሄዱን አንስተው ነገር ግን በዚህ ብቻ ሳይገደብ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ተንቀሳቅሶ ለመስራት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ በበኩላቸው እንደ ሀገር በርካታ ችግር ፈቺ የሆኑ የሀገር በቀል እውቀቶች ቢኖሩንም በህብረተሰቡ ዘንድ በነበረው የአመለካከት ችግሮች እና ቀደም ሲል የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ስላልነበር በዘርፉ ተጠቃሚ ሳንሆን ቆይተናል ብለው በአሁኑ ወቅት እንደ አዲስ በተነደፈው የእድገት ፍኖተ ካርታ መሰረት ለሀገር በቀል ዕውቀቶች ከፍተኛ ትኩረት በመሰጠቱ ዩኒቨርሲቲዎች ምርምሮችን እና ጥናቶችን እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ፕ/ር ዮሴፍ ማሞ ሲናገሩ የሀገር በቀል እውቀት ማለት በማህበረሰቡ ውስጥ ለዘመናት በግልጋሎት ላይ ሲውሉ የነበረና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፊ የመጣ እውቀት ማለት መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የከተሞች መስፋፋትንና ዘመናዊነትን ተከትሎ እነዚህ የራሱ የማህበረሰቡ የሆኑ ዕውቀቶች ትኩረት ተነፍጓቸው መቆየታቸውን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት እነዚህ እውቀቶች ከዘመናዊ አሰራሮች ጋር የሚስማሙ እንዲሆኑ ምርምሮችን ማካሄድ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በመጨረሻም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሲዳማ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ እንደተናገሩት መንግስት እነኚህ እውቀቶች በዘላቂነት የሀገሪቱን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚገባውን አስተዋፅኦ ይወጡ ዘንድ በፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ውስጥ በማካተት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል። ተቋሙ በሲዳማ ህዝብ ባህል፣ ቋንቋ፣ ባህላዊ ህክምና እና የግጭት አፈታት ዘዴዎች ላይ ምርምር ማካሄዱንና በዚህ ምክክር ዝግጅት ላይም በምርምሩ ወቅት የተገኙ ውጤቶች እንደሚቀርቡና እንደሚተቹ እንዲሁም የተቋሙ የወደፊት የጥናትና ምርምር ትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ ግብዓቶች እንደሚሰበሰቡ አብራርተዋል።