የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ እና ኮምፒቲሽናል ሳይንስ ኮሌጅ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያስተምሩ ሴት መምህራንን በሳይንስ፣ በምርምር እና መሪነት ዙሪያ ማብቃት በሚል ርዕስ የምክክር አውደ ርዕይ አዘጋጅቷል፡፡
የአውደ ርዕዩ መድረክ የተካሄደው በግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም በወንዶ ገነት የደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ግቢ ሲሆን በርካታ የኮሌጁ መምህራንና ሠራተኞች ተሳትፈውበታል፡፡
ዶ/ር ዘይቱን በጋሻው የተፈጥሮ እና ኮምፒቲሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን የፕሮግራሙን ዋና ዓላማ ሲገልጹ አዲስ የተቀጠሩት መመህራን ከነባሮቹ መመህራን የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ፣ ሴቶች በሳይንስ፣ በምርምር እንዲሁም በአመራር ደረጃ እራሳቸውን ማብቃት እንዲችሉና በሚያጋጥማቸው ችግሮቻቸውና መፍትሄዎቻቸው ላይ ምክክር ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዘይቱን አክለውም በኮሌጃችን ሴት መምህራንን በዝውውር፣ በቅጥር እና አብላጫ ውጤት ያመጡ ተመራቂዎችን በማወዳደርና በመቅጠር ከአምስት ዓመት በፊት 5 የነበረው የሴት መምህራኖቻችን ቁጥር በአሁኑ ሰዓት 53 የደረሰ ሲሆን መምህራኖቻችንም በተፈጥሮ ከተሰጣቸው ትውልድን የመተካት ጸጋ እንዳለ ሆኖ ውጤታማ መሪ፣ መምህር እና ተመራማሪ እንዲሆኑ የሚሰጣቸውን እድል በመጠቀም እራሳቸውን ማብቃት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ዙፋን በደዊ የተፈጥሮ እና ኮምፒቲሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ባይሎጂካል ሳይንስ ዲን በበኩላቸው እንደተናገሩት ሴቱች እራሳቸውን ለማብቃት ትስስር መፍጠር፣ በየጊዜው በመገናኘት ምክክርና ውይይት ማድረግ፣ ውድድር መፍጠር እና ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሄዎችን ለማምጣት አንድነትና መተባበር ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡
እንዲሁም መምህርት ስመኝ ስርካ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክ/ሽግግር አስተባባሪ እንደገለጹት የሴት መመህራኖቻችን ቁጥር ከበፊቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ነባር መምህራን ለአዲሶቹ አርአያ በመሆንና ከመደበኛው የገጽ ለገጽ ውይይት በተጨማሪ ቴክኖሎጂ የፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ኢ-መደበኛ ትስስር ሊመሰረት ይገባል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የተለያዩ ጥናታዊ ጹሁፎችና ሰነዶች ቀርበው ውይይትና ምክክር ከተሳታፊዎች ጋር ተካሂዶ ፕሮግራሙ መጠናቀቁ ታውቋል፡፡