በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግንቦት 13 እና 14 ቀን 2013 ዓ.ም የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕ/ጽ/ቤት የማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ስልጠና አዘጋጅቷል፡፡
ስልጠናው የተዘጋጀው በዩኒቨርስቲው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ሲሆን በስልጠናው ለይ የተገኙት የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ፍሬው ካሳ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም ዩኒቨርሲቲው ለሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ስልጠናዎችን የሰጠ እና የማቴራያል ድጋፍ ያደረገ መሆኑን ጠቁመው የአሁኑ ስልጠና በከተማ አስተዳደሩ ስር ከሚገኙ ከሐይቅ ዳር፣ ባህል አደራሽ፣ መሀል እና ምስራቅ ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ 50 ጎዳና ተዳዳሪዎች የተሰጠ የአቅም ግምባታ የመጀመሪያ ዙር ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል። ሲያጠቃልሉም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በተገባው ውል መሰረት ለ250 ጎዳና ተወዳዳሪዎች እና ስራ አጥ ወጣቶች በሶስት ዘርፎች ማለትም በዶሮ እርባታ፣ በከተማ ውበት እና በጫማ መጥረግ/ሊስትሮ ስራ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እና የማቴራያል ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
በማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የትምህርትና ስልጠና ባለሙያው አቶ ጌታቸው ያዬ በበኩላቸው የዛሬው ስልጠና ዳይሬክቶሬት መስሪያ ቤታቸው ላለፉት ተከታታይ ዓመታት በከተማ አስተዳደሩ ስር ለሚገኙ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሲሰጥ ከነበራቸው ስልጠናዎች የቀጠለ መሆኑን ጠቅሰዋል። ስልጠናው የተዘጋጀው ጎዳና ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ አካላት አሁን ካሉበት ሁኔታ ወጥተው ስራ ፈጣሪ ዜጋ በመሆን ከጥገኝነት ተላቀው የራሳቸውን ህይወት እንዲመሩ ለማስቻል የሚሰጥ የአቅም ግንባታ ስልጠና ነው ካሉ በኋላ እነዚህ በጎዳና ላይ ህይወታቸውን እየመሩ ያሉ ልጆች የማህበረሰቡ አንድ አካል ስለሆኑ ሳይንሳዊ የሆነ ስልጠና እና ድጋፍ ካገኙ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር ነገያቸውን የማየት ሕልም ይኖራቸዋል ብለዋል።
የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የእንስሳት እርባታ እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ባለሙያ የሆኑት አቶ ጋሻው ቢኖ ቀደም ሲል በሲዳማ ክልል በለኩ እና ሀዋሳ ከተማ በሚገኙት ዳቶ እና ጨፌ ኮቲ ጀቤሳ በዶሮ እርባታ ዘርፍ ለሰለጠኑ ስራ አጥ ወጣቶች ጫጩት እና መኖን ጨምሮ ለእያንዳንዱ ሰልጣኝ የአንድ ሺ አምስት መቶ ብር ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደስራ መግባታቸውን ገልፀዋል። አሁን ስልጠና ላይ ለሚገኙ እና በጫማ መጥረግ/ሊስትሮ ስራ ላይ ለሚሰማሩ የሊስትሮ ሼዶች በጨረታ ሂደት ላይ እንዳሉ አንስተው የከተማውን ውበት በጠበቀ መልኩ ተመቻችተው ለሰልጣኞች እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።