በJhpiego ድጋፍ ለስምንት የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አውደ ርዕይ ተዘጋጅቷል፡፡ ግንቦት 6 እና 7 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው አውደ ርዕይ ከዩኒቨርሲቲዎች ጤና ሳይንስ ኮሌጆች፣ የአጋር ተቋማት ተወካዮች፣ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።
በተካሄደው በዚሁ ዝግጅት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አንተነህ ጋዲሳ ኮሌጁ ምስረታውን ካደረገበት ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በየጊዜው ደረጃውን በማሳደግ የትምህርት ክፍሎቹን እና የሚቀበላቸውን የተማሪዎችን ቁጥር እየጨመረ መቷል ብለዋል። ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት የስፔሻሊቲ፣ የድህረ ምረቃ እና የፒ.ኤች.ዲ ፕሮግራሞች ያሉት ሲሆን በኮምፕሬንስቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ደረጃ ከ450 በላይ አልጋዎች ያሉት እና 20 ሚሊዮን ለሚጠጉ የማህበረሰብ ክፍሎች በቋሚነት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከመደበኛ ሕክምና ጎን ለጎን በአሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ማዕከል በመሆን እያገለገለ ይገኛል ብለዋል። አክለውም ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪ ኮሌጁ በምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ንቁ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው ይህ አይነቱ ከአቻ ኮሌጆች ጋር የሚደረገው የልምድ ልውውጥ ይህንን ተግባሩን እጅግ በላቀ ደረጃ ለማሳደግ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል። የዛሬው የልምድ ልውውጥ ዋና አላማ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያሉ ውጤታማ ልምዶችን በመለዋወጥ የመማር ማስተማሩን ጥራት ለማሻሻል፣ የመማሪያ ክፍሎችን እና ላብራቶሪዎችን ለማዘመን እንዲሁም በጋራ ስለመስራት መምከር እንደሆነ ተናግረዋል።
የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ ትምህርት ጥራት ቁጥጥር እና ማረጋገጫ አስተባባሪ ዶ/ር አለማየሁ ቶማ በበኩላቸው ኮሌጁ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እና ለማሳደግ በብዙ መልኩ የተለያዩ ተግባራትን መከወኑንና ከእነዚህም መካከል ተመሳሳይነት ያላቸውን የትምህርት ክፍሎች የላብራቶሪ አገልግሎትን በጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ የሀብት ብክነትን ለመቀነስ መቻሉን፣የተማሪዎች ፈተና አሰጣጥና ምዘናን በማሳደግ፣ የመማርያ ክፍሎችንና የትምህርት ግቢውን ለተማሪዎች ምቹና ተስማሚ ለማድረግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን እና በዚህም አመርቂ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል። ለዚህ ስራም የJjpiego ድጋፍ አይነተኛ እንደነበር ገልጸው የዛሬው ልምድ ልውውጥ በሌሎች ኮሌጆች ያሉ ውጤታማ ልምዶችን በመካፈል ያሉብንን ክፍተቶች ለማረም ይረዳናል ብለዋል።
በዝግጅቱ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የትምህርት ጥራት እና ማረጋገጫ አስተባባሪው ረ/ፕ/ር ረታ ፀጋዬ ሀሳባቸውን ሲሰጡ ዩኒቨርሲቲያቸው የአዲሱ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ መጠን ነባር ከሆኑና በርካታ ልምድ ካላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚደረገው የልምድ ልውውጥ በእጅጉ እንደሚጠቅማቸው ተናግረዋል። ዛሬ በተካሄደው የላብራቶሪ ጉብኝት በርካታ አዳዲስ ልምዶችን መካፈላቸውን ገልጸው ይህንን እና ሌሎች ውጤታማ የሚያደርጉ ልምዶችን ወደ ኮሌጃቸው ለመውሰድ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በመጨረሻም ተሳታፊዎች በኮሌጁ ተገኝተው ስለተመለከቷቸው ነገሮች ሀሳባቸውን ያጋሩ ሲሆን፣ ተዘዋውረው ባዩትና በተደረገላቸው ገለጻ መደሰታቸውን እና ዩኒቨርሲቲው የጀመራቸውን ውጤታማ ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። እያንዳንዱ ተሳታፊም የየራሱን ልምዶች በማካፈል በትብብር ሊሰራ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ምክክር ተደርጓል፡፡