ከግንቦት7-8 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕ/ጽ/ቤት ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ስልጠናው በአእምሯዊ ንብረት መብት ደንቦችና መመሪያዎች፣ በመረጃ አፈላለግ፣ በቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ድጋፍ ዙሪያ ሲሆን ከተለያዩ የስራ ክፍሎች የተውጣጡ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ዶ/ር ታፈሰ ማቲዮስ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲያችን ረጅም የምርምር ታሪክ እና ከተወሰኑ ዓመታት ጀምሮ ደግሞ በቴክኖሎጂና ፈጠራ፣ ሽግግርና ማስፋት ዙሪያ ትኩረት በመስጠት ለተመራማሪዎችና ለተማሪዎች ድጋፍ በማድረግ በርካታ ስራዎች እየሰራ ቢሆንም በዩኒቨርሲቲው የአእምሯዊ ንብረት መብት ደንቦችና መመሪያዎች ባለመኖራቸው ዩኒቨርሲቲውም ሆነ ተመራማሪዎቹ በቂ በሚባል ደረጃ ተደራሽና ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ስልጠናው ማስፈለጉን ተናግረው ከዓለም አቀፍና ከኢትዮጵያ የአእምሯዊ ንብረት መብት ደንቦችና መመሪያዎች በመነሳት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በተዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ ላይ በመወያየት ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ ማመላከትና በኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት የተሰሩና እየተሰሩ ባሉ ስራዎች፣ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ በመክፈቻው ላይ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ባዩ ቡንኩራ የኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው ዳይሬክቶሬቱ የተቋቋመበትን ዓላማ፣ እስካሁን የሰራቸውን እና እየሰራ ያለውን ተግባራት በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ሶስት የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያዎች በመክፈት ተማሪዎች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ልምምድ እንዲያደርጉ ድጋፎችን እያደረገ እንደሆነ እና ተመራማሪዎችም አስፈላጊው ድጋፍ እተደረገላቸው በርካታ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማድረግ ለህብረተሰቡ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ለሚገኙ የኒቨርሲቲዎች ማስተማሪያ የሚሆን የምህንድስና ሀይድሮሊክ ማሽን በሽያጭ በማስረከቡ እንደሀገርም ከውጭ የሚገቡትን የማስተማሪያ መሳሪያዎች በማስቀረት የውጭ ምንዛሪን ማስቀረቱን ገልጸዋል፡፡