የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጽ/ቤት በማህበረሰብ አግልግሎት ዘርፉ ያዘጋጀውን ስልጠና ሚያዚያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ሰጥቷል፡፡
በዚሁ ስልጠና ላይ የተገኙት የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ፍሬው ካሳ ዳይሬክቶሬቱ ለሲዳማ ክልል እና ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ወቅቶች በግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ጤና እና ምግብ አጠባበቅ እንዲሁም የትምህርት ዘርፎች በርካታ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይህ ዛሬ እየተሰጠ ያለው ስልጠና ከእነዚህ መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የዛሬው ስልጠና በከተማ አስተዳደሩ ስር ከሚገኙ 13 የመንግስት ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ 26 የሳይንስ መምህራን የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም የዛሬው ስልጠና በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው በባዬሎጂ እና ኬሚስትሪ የትምህርት ዘርፎች ላይ መሆኑንና ለእነዚህ የትምህርት ዘርፎች አስፈላጊ በሆነው የላብራቶሪ አጠቃቀም ላይ ሰልጣኞች የተሻለ እውቀት እንዲኖራቸው እንዲሁም ይህን ያገኙትን እውቀት ለሌሎች መምህራንና ለተማሪዎቻቸው እንዲያጋሩ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ከስልጠናው በተጨማሪም አስፈላጊ የሆኑ የላብራቶሪ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል መግባቱን ተናግረዋል።
በማህበረሰብ አግልግሎት ዳይሬክቶሬት የትምህርት እና ስልጠና ባለሙያ የሆኑት አቶ ጌታቸው ያዬ በበኩላቸው ስልጠናው የመጀመሪያ ዙር መሆኑንና በዚህ የሚያበቃ እንዳልሆነ ገልጸው በቀጣይ በሌሎች የትምህርት መስኮችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው በቅርቡም የአስተዳደር አካላት የሆኑትን ርዕሰ መምህራን እና ሌሎች የአስተዳደር ሰራተኞችን የያዘ ስልጠና እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
በመጨረሻም በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የትምህርት መምሪያ የትምህርት አመራር ልማት ስራ ሂደት ባለሙያ የሆኑት አቶ ገዛኸኝ ደገፉ የማህበረሰብ አገልግሎት ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ስልጠና እና ድጋፍ ሲያደርግ የነበረ መሆኑን አስታውሰው ዛሬ እየተሰጠ ያለው ስልጠና የመምህራንን አቅም ከማሳደግ አንፃር አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግዋል። ትምህርት መምሪያው በተለያዩ ወቅቶች የስልጠና ፕሮፖዛሎችን ቀርጾ ለዩኒቨርሲቲው ማስገባቱን እና ዩኒቨርሲቲውም አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ ስልጠናዎቹን ሲሰጥ ስለነበር ምስጋናቸውን አቅርበው ይህ ትብብርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።