በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በእምቦጭ መጤ አረምና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ የምክክር አውደ ጥናት ተካሄደ

የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጥናት ማዕከል ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬ/ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በእምቦጭ መጤ አረምና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምክክር አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

ሚያዚያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደው በዚሁ የምክክር አውደ ጥናት ላይ የተገኙት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን የእምቦጭ አረም በ1950ዎቹ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባና መጀመሪያ አባ ሳሙኤል በሚባለው የውሀ ማጠራቀሚያ እንደታየ ገልጸው አረሙ በመቀጠልም ወደ ቆቃ ሀይቅ እንደተዛመተ እንዲሁም ጥንቃቄ ባለመደረጉ በአሁኑ ሰዓት የዝዋይና አባያ ሀይቆችን ወሮ እንደሚገኝ አብራርተዋል። እንደ ሀዋሳ ሀይቅ ያሉ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች በአረሙ የመወረር ከፍተኛ ስጋት እንዳለባቸው ጠቁመው ይህ ከመከሰቱና ጉዳቱ መመለስ ከማይችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ፈጣንና የተቀናጀ የቁጥጥር ስራ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

አክለውም ይህን ችግር የተረዳውና በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚጠበቅበትን ለማድረግ ከፊት እንደተሰለፈና ሌሎችም በስምጥ ሸለቆው ዙሪያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ለዚህ ችግር መቀረፍ በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ አሳስበዋል። ከዚህ የምክክር አውደ ጥናት ሶስት ዋና ዋና ውጤቶች ማለትም የስምጥ ሸለቆ ሀይቆችን ከመጤ እምቦጭ አረም ለመከላከል የሚያስችል ረቂቅ፣ በሁሉም እህት ዩኒቨርሲቲዎች ሲካሄዱ የነበሩ የእምቦጭ አረምን የመቆጣጠር ስራዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን የመለየትና ከእህት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን እና የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ባለስልጣን ጋር የትብብር ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጥናት ማዕከል ዋና ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ጌታቸው ስሜ  ስለምክክር አውደ ጥናቱ ሲያስረዱ ይህ መድረክ በስምንት በስምጥ ሸለቆ ዙሪያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል እውቀትንና ልምድን ለመለዋወጥ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል። አካባቢው የበርካታ ዉሀ ሀብቶች ባለቤት የሆነና ለአካባቢው ህብረተሰብ ህይወት መሰረት የሆነ ቢሆንም እኚህ የውሀ አካላት ባልተገባ የሰው ልጅ ድርጊቶች ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛል ብለዋል። በዋናነትም የወንዞችና ሀይቆች በዚህ መጤ አረም መወረር በስነ-ምህዳሩና የሰዎች ህይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ መደቀኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም ይህ መጤ የእምቦጭ አረም ከፍተኛ የውሀ መትነንን በመፍጠር፣ የጀልባ እንቅስቃሴንና የአሳ ማስገር ስራውን በመገደብ በውሀ ስርዓቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ብለዋል። ማዕከሉም ይህን አሳሳቢ ችግር በመረዳት የሀዋሳን እና ስምንቱን በስምጥ ሸለቆ ዙሪያ የሚገኙትን የአርባምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ አርሲ፣ ወልቂጤ፣ ወራቤ፣ ዲላ፣ ቡሌ ሆራ እና ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን እና የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ልማት ጽ/ቤት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ይህን የምክክር መድረክ ማዘጋጁቱን ገልጸዋል።

በመጨረሻም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ግርማ ጥላሁን በበኩላቸው የሀዋሳ ሀይቅ በአካባቢው እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ጎብኚዎች ያሉትና በዙሪያው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የገቢ ምንጭ የሆነ ሳቢ ሀይቅ መሆኑን ገልጸው ነገር ግን ሀይቁ እየሰጠ ባለው አግልግሎት ልክ በቂ ጥበቃ እየተደረገለት እንዳልሆነ ተናግረዋል። ይህ ምክክርም የሀዋሳ እና ሌሎች የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች በመጤ እምቦጭ አረም የተጋረጠባቸውን አደጋ እና በመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደሚያስችል ገልፀዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et