የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በግብርና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ በተዘጋጀው ሀገር በቀል የተቀናጀ የፒኤችዲ ፕሮግራም ስርዓተ-ትምህርት ላይ ውጫዊ ግምገማ አካሄደ

በቀን 02/08/2013 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ ሮሪ አለም አቀፍ ሆቴል በተካሄደው በዚሁ ግምገማ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት

ሳይቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ፋሲካ ቤቴ በሀገራችን የሚካሄደው የግብርና አመራረት አነስተኛ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም፣ የመሰረተ ልማትና የገበያ ትስስር እጥረት ያለበት፣ በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነ እና አነስተኛ ምርት የሚገኝበት መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን የሀገራችን የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን ይህን ዘርፍ ለማዘመን ትምህርት የማይተካ ሚና እንዳለው በማመን መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አክለውም የመጀመሪያው ትውልድ የምርምር ዩኒቨርሲቲ የሆኑት የሀዋሳ እና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች በሀገር ደረጃ ከፍተኛ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት የሚታይበትን የግብርና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ለማሻሻል የተዘጋጀውን ሀገር በቀል ስርዓተ-ትምህርት ውስጣዊ ግምገማ በመጨረስ በዛሬው እለት የጋራ ውጫዊ ግምገማ እያካሄዱ ይገኛል ብለዋል። ይህ የፒኤችዲ ፕሮግራም በግብርና ማሺነሪ እና የመሬትና ውሃ ጥበቃ ላይ ትኩረት በማድረግ በሀገር ጀረጃ የተማረ የሰው ኃይል እጥረቱን ለመቅረፍ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑን አብራርተው ሲያጠቃልሉ ሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች የዚህን ስርዓተ-ትምህርት ረቂቅ በማዘጋጀቱ ሂደት በተለያየ  ደረጃዎች ማለፋቸውን ጠቁመው ለግምገማው አዘጋጆችና ከሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከሲዳማ ብ/ክ/መ እና የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ ለተገኙ ተሳታፊዎች ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የድህረ ምረቃ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አለማየሁ ሙሉነህ በበኩላቸው ስርዓተ-ትምህርቱ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለዚሁ ፕሮግራም ለተመረጡ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች መላኩን ገልጸዋል። የሀዋሳ እና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎችም ለዚሁ ፕሮግራም ስለተመረጡ የመጀመሪያውን ውስጣዊ ግምገማ አጠናቀው በዚያም የተገኙ ግብዓቶችን ጨምረው ለውጫዊው ግምገማ መገኘታቸውን አስረድተው በውጫዊ ግምገማው የሚገኙ ውጤቶች እንደግብዓት ተጠቃለው ለዩኒቨርሲቲ አመራሮች እንደሚቀርቡና እንደሚፀድቁ ገልጸዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ ኃላፊው አቶ ታምሩ ተስፋዬ የዚህ ፕሮግራም መጀመር በአምስት አመታት ውስጥ (በ2025) 5000 የፒኤችዲ ተማሪዎችን ለማፍራት ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል። መንግስት ከመረጣቸው ከአምስቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ማለትም ግብርናና ማኑፋክቸሪንግ፣ አይ.ሲ.ቲ፣ ቱሪዝምና ማይንግ ዘርፎች መካከል አንዱ ግብርና በመሆኑ በዚሁ ዘርፍ የታለመውን ውጤት ለማምጣት የዚህ ፕሮግራም መጀመር አይተኬ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። ይህ ፕሮግራም ሲጀመር ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 65 ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ 45 ተማሪዎችን ተቀብለው በፒ.ኤች.ዲ እንደሚያስተምሩ ገልጸዋል።

በመጨረሻም በዕለቱ በቀረበው ስርዓተ-ትምህርት ላይ ሰፊ ገለፃ እና ጥልቀት ያለው ውይይት ተካሂዷል።

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et