ሚያዝያ 2 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው በዚሁ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪውቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አንተነህ ጋዲሳ በመክፈቻ ንግግራቸው ኮሌጁ ስራ
ከጀመረበት ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በህክምናው ዘርፍ የተጣለበትን ኃላፊነት ከግብ ለማድረስ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት በክልላችንም ሆነ በሀገር ደረጃ ያለውን የህክምና ባለሙያ እጥረት ለመቀነስ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
አያይዘውም ዛሬ ኮሌጁ ያስመረቃቸውን 222 ዶክተሮችን ጨምሮ ከ2001-2013 ዓ.ም 1,551 የህክምና ዶክተሮች ያስመረቀ መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ጊዜ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ጭምር ህብረተሰቡን እያገለገሉ መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም ኮሌጁ ከመማር ማስተማር በተጨማሪ በኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ደረጃ ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የክልላችንና የአጎሪባች ክልሎች ማህበረሰብ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ከመደበኛው ህክምና ጎን ለጎን በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ እንዲሁም በሀገራችን ተከስቶ ያለውን ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከልና ለማከም የራሱን ኃላፊነት በመወጣት ላይ መሆኑን ገልፀዋል። ሲያጠቃልሉም ለ12ኛ ዙር በህክምና ዶክትሬት ዲግሪ ከተመረቁት ውስጥ 73 ያህሉ ሴቶች መሆናቸውንና በሌላ በኩል በተለያዩ የስፔሻሊቲ ትምህርት ክፍሎች 48 ያህል ስፔሻሊስት ሀኪሞች ለ5ኛ ዙር ከተመረቁት መሀል 7ቱ ሴቶች መሆናቸውን ገልፀዋል። ተመራቂዎቹም ዛሬ የሚገቡትን ቃል አክብረው በጊዜያዊ ቾግር ተስፋ ሳይቆርጡ ዕርዳታ ፈልገው የሚመጡ ህመምተኞችን በቅንነት የማገልገል አደራ እንዳለባችው አሳስበዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይና አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ኢ/ር ፍስሐ ጌታቸው በበኩላቸው ለተመራቂ ተማሪዎች፣ ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች፣ ለተማሪ ቤተሰቦችና ለኮሌጁ ማህበረሰብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ የህክምና ትምህርት ብዙ ዓመታትን በጽናትና በብቃት መወጣትን የሚጠይቅ በመሆኑ የአሁኑ ተመራቂዎችም ይህን አልፈው የመጡ በመሆናቸውና የዘንድሮ ተመራቂዎች ትምህርቱ ከሚጠይቀው ቁርጠኝነት በተጨማሪ የወቅቱ የሀገራችንና የዓለማችን ፈተና ሆኖ ከሚገኘውን ከኮሮና ቫይረስ ጋርም በመታገል ለዚህ የደረሱ ናቸው ብለዋል። አያይዘውም በአሁኑ ወቅት የህክምና ባለሙያዎች ቫይረሱን በመከላከል ረገድ እያሳዩ ያሉት ተጋድሎ በማንም ዘንድ የማይዘነጋ መሆኑንና ዛሬ የሚመረቁ ተማሪዎችም ኮሮናን እንዲሁም ሌሎች በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
በመጨረሻም የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የሀዋሳ ከተማ ም/ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ለተመራቂ ተማሪዎች ዲግሪያቸውንና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ደግሞ ሽልማት ስጥተዋል። ቀጥለው ባሰሙት ንግግርም ትምህርት የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን አስታውሰው ተመራቂዎቹን በየደረጃው በሚከሰተው ማዕበል ወደ ኋላ ሳይሉ የሚገጥማችሁን ፈተና ሁሉ በአሸናፊነት እንደሚወጡ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።