መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ የተማሪዎች ህብረት መማክርት ምርጫ በዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን በቦታው የተገኙት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ከበደ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ ይህ ምርጫ ቀደም ሲል መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ አሁን ላይ ለመደረግ እንደበቃ ገልጸዋል።
አሁን ምርጫ የሚካሄደው በየትምህርት ክፍሎቻቸው የመመረጫ መስፈርት የሆነውን 2.75 እና ከዚያ በላይ CGPA አሟልተው ከተወከሉ ዘጠና የፓርላማ አባላት ተማሪዎች መካከል መሆኑንና የምርጫው አርባ በመቶ ቀደም ብሎ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪው ስድሳ በመቶ አሁን እንደሚከናወን ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም እጩዎች በያዙት እቅድ፣ አቀራረብ፣ ባላቸው የራስ መተማመንና ሌሎች መስፈርቶች እንደሚመዘኑ ገልጸው መራጮች ከየትኛውም የብሄር እና ሌሎች አመለካከቶች ተላቀው በምክንያታዊነት ላይ ብቻ በመመስረት የተሻለውን እጩ እንዲመርጡ አሳስበዋል። ተመራጮችም የሚቀበሉት ኃላፊነት ትልቅ መሆኑን በመገንዘብ የሚያገኙትን እድል በአግባብ መጠቀም እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
አስመራጭ ኮሚቴዎችን የወከሉት አቶ አባይ አለማየሁ በበኩላቸው በዛሬው ዕለት በሚኖረው ምርጫ የፓርላማ አባላት ሶስት ተማሪዎች የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሆነው እንደሚመረጡ ገልጸዋል። ስምንት ተማሪዎች ለስራ አስፈጻሚነት እጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን መራጮችም ይወክለናል የሚሉትን እጩ ለእያንዳንዱ እጬ በተሰጠው ኮድ ላይ ውጤት በመስጠት መምረጥ እንደሚችሉ አብራርተዋል። ስምንቱ የስራ አስፈፃሚ አራቱ የአፈ ጉባኤና ኦዲት እጩ ተወዳዳሪዎች የየራሳቸውን እቅድ እና ስትራቴጂ ያቀረቡ ሲሆን ይህን ተከትሎም በተካሄደው ምርጫ አሸናፊ የሆኑ ሶስት ስራ አመራር ኮሚቴ፣ ሁለት አፈ ጉባኤና ሶስት ኦዲት ኮሚቴዎች ተመርጠዋል።
በመጨረሻም የዋናው ግቢ ተማሪዎች አገልግሎት ዳይሮክቶሬት ዳይራክተሩ በምርጫው ሂደት ዙራያ ባዩት ነገር መደሰታቸውን ጠቅሰው ተመራጮች በመማር ማስተማሩ በዋናው ግቢ ተማሪዎችና በማህበረሰብ መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት በማስፋት በግቢው ሰላምና ፀጥታ ላይ የላቀ ውጤት ያመጣሉ የሚል እምነተ እንዳላቸው ተናግረዋል።