ከመጋቢት 9/2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተደረገው የውይይትና የምክክር መድረክ መክፈቻ ላይ ዶ/ር አያኖ በራሶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እንደተናገሩት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከተቋቋመ ጀምሮ የሳይንስና ከፍተኛ
ትምህርት ሚኒስቴር አዋጅ፣ደንቦች፣መመሪያዎችና ፖሊሲዎች ወጥተው ተግባራዊ የሆኑ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በቅርቡ ተግባራዊ የሆኑ እና በሚሆኑ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና የ10 እና 5 ዓመት ዕቅድ ላይና በዩኒቨርሲቲው የ10 እና 5 ዓመት ዕቅድ ላይ ከከፍተኛ፣ ከመካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች ጋር ለመወያየት እና ለመምከር መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ከሁሉም መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ጋርም ውይይጥ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ አክለውም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብለው ከተለዩት አንዱ እንደመሆኑ የቀጣይ 10 ዓመት ዕቅድ ስናዘጋጅም ምርምርን መሰረት በማድረግ እና የልህቀት ማዕከሎች ከማጎልበት አንጻር ሲሆን አመራሮች በስራቸው ያለውሉትን ስራዎችና ሰራተኞች በአግባቡ ለማስተዳደር በዕለቱ የቀረቡትን የማስፈጸሚያ ስልቶች መረዳትና ማወቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
በዕለቱ የከፍተኛ ትምህርት ያቀረቡት ዶ/ር ፍስሃ ጌታቸው እንደተናገሩት ባለፉት 20 ዓመታት ዩኒቨርሲቲዎች እየተስፋፉ የመጡ ቢመጡም የዛኑ ያክልም ከአግባብነት፣ ከተደራሽነት፣ ከአካታችነት፣ ከትምህርት ጥራትና የፖሊሲ አቅጣጫ ከማስቀመጥ አኳያ ችግሮች በመኖራቸው ገበያው የሚፈልገውን እና አካታች የሆነ የሰው ኃይል በበቂ ቁጥርና ጥራት ማፍራት አለመቻሉን ተናግረው ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ጥራትና ብቃት ያላቸውን ምሩቃኖች ለማፍራት ብቃት ያላቸውን መምህራንን በመቅጠርና ብቃታቸውን ለማሳደግ እና ገበያው የሚፈልገውን ምሩቃንን ከማፍራት አንጻር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ የምርምርና ቴ/ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት የሳይንስ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሰነድን ባቀረቡ ወቅት የኢትዮጵያ ሳይንስ ፖሊሲ የትኩረት መስኮች የሰው ሃብት ልማት፣ የኢንተርፕራይዝ ልማት፣ ሳይንሳዊ ምርምርና ፈጠራ፣ መሰረተ ልማትና ግብዓት፣ የእውቀት/ሀብት አያያዝ ስርዓት፣ ፋይናንስና ማበረታቻ ስርዓት እና ሃገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ አጋርነት መሆናቸውን ገልጸው በየአንዳንዱ ስርም የሚገኙትን የተለያዩ ግቦችና የማስፈጸሚያ ስልቶችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
ከቀን 13/07/2013 ዓ.ም ጀምሮም በየደረጃው ያለ የዩኒቨርሲቲው ማ/ሰብ ለሁለት ቀናት ውይይቱን የቀጠለ ሲሆን በርካታ ተሳታፊ እየተከታተለ እንዳለ መረጃው ያመለክታል፡፡