ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ኮሌጅ በሳይንሳዊ የወረቀት አፃፃፍ ክህሎት ላይ በዋናው ግቢ በ03-07-2013 ዓ.ም ስልጠና በሰጠበት ወቅት በቦታው የተገኙት የትምህርት ኮሌጁ የትምህርት እና ቴክኖሎጂ ስርፀት ተባባሪ ዲን ዶ/ር ማርቆስ መኩሪያ
በንግግራቸው የትምህርት ኮሌጁ ወደ ኮሌጅ ደረጃ ከማደጉ በፊት ትምህርት እና ስልጠና ይባል እንደነበረ ገልፀው ወደ ኮሌጅ ካደገበት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመማር ማስተማሩ፣ በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ላይ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ተባባሪ ዲኑ አክለው ሲናገሩ ኮሌጁ የምርምር ሥራውን ሳይንሳዊና ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ በማለም ይህ ስልጠና እንደተዘጋጀ አብራርተው በዚህ ስልጠና ለይ ተሳታፊ የሆኑ መምህራንና ተመራማሪዎች ምርምሮቻቸውን ሳይንሳዊ በማድረግ ረገድ በቂ ክህሎት እንደሚያገኙና በዚህም በርካታ የምርምር ሥራዎችን በውጤታማነት እንደሚያጠናቅቁ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
የትምህርት ኮሌጅ ዕቅድና ሥራ አመራር አካቶ ዘርፍ ተባባሪ ዲን የሆኑት ዶ/ር አንተነህ ዋሲሁን በበኩላቸው ተሳታፊ ሰልጣኞች በኮሌጁ ውስጥ ከሚገኙ አራት ት/ክፍሎች የተወጣጡ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ስልጠናው የምርምር ሥራዎቻቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማሳተሙ ላይ የሚታየውን ክፍተት ይሞላል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ ስልጠናው በዚህ ብቻ ሳይገደብ ተመሳሳይና ሰፋ ያለ ስልጠና ለሁሉም መምህራን የሚሰጥበት ሁኔታ ቢመቻች ተመራማሪዎች የተሻለ እውቀት የሚያገኙ ሲሆን ሃገሪቱም በዚሁ ዘርፍ ተጠቃሚ ትሆናለች ብለዋል።
በመጨረሻም በዕለቱ ስልጠናውን የሰጡት የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ኃላፊ ፕ/ር ተስፋዬ ሰመላ ሲናገሩ በስልጠናው የተሳተፉ መምህራኖች ከስልጠናው የሚያገኙአቸውን ክህሎቶች በአግባቡ በመጠቀም በሚያከናውኑአቸው ምርምሮች ላይ የተሻለ ውጤታማነትን ሊያመጡ እንደሚገባ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።