የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ኮምፒዩቲሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ባለቁና በሂደት ላይ ባሉ የምርምር ስራዎች ላይ የሚያካሂደውን ግምገማ ሐሙስ የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለ2 ቀናት ያካሄደ ሲሆን በወቅቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሌጁ

ዲን ዶ/ር ዘይቱ ጋሻው ለመጀመርያ ጊዜ እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ግምገማ ላይ ለታደሙ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። በመቀጠልም ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ለህይወት መሰረታውያን መሆናቸውን አንስተው በዚህም የተነሳ በዓለም ላይ የሚገኙ ሀገሮች ሁሉ በዚሁ ዘርፍ የምርምር ስራዎችን በመንደፍ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል። ባለፉት መቶ አመታት ዓለማችን በዘርፉ በርካታ እምርታዎችን ማስመዝገቧን እና በአሁኑ ወቅት የምንመለከታቸው አብዛኛዎቹ ግኝቶችም የዚሁ ማስረጃ ናቸው ብለዋል። ይህ ሁሉ እመርታ ቢመዘገብም ግን አሁንም ድረስ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚስተዋለው የህዝብ ቁጥር መጨመርና ድህነት ከፊት ተደቅኖ የሚገኝ ፈተና ስለሆነ ይህን ለመቅረፍ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሁለተኛ አብዮት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ኮሌጁ የሚገጥሙ ችግሮችን ለማለፍ በቁርጠኝነት እየሰራ ሲሆን ትኩረቱንም በባዬሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ስፖርት ሳይንስ፣ በመሬት እና ሒሳብ ሳይንስ ላይ አድርጎል። በኮሌጁ የተለያዩ ፋካሊቲዎች ሰራተኞችም በበርካታ ፈታኝ የምርምር ስራዎች ላይ በመሳተፍ እና ግኝቶችን  በማሳተም ላይ ይገኛሉ ብለዋል። ኮሌጁ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ከበርካታ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይህ ግምገማም አለማ አድርጎ የተነሳው በሂደት ላይ ያሉ የምርምር ስራዎችን ለመመልከት እና ለተመራማሪዎች ክፍተት ባሉበት ቦታዎች ላይ ጠቃሚ ግብዓቶችን እንዲያገኙ ነው ብለዋል። ንግግራችውንም ሲያጠቃልሉም ለዚህ ፕሮግራም መሳካት አስተዋጽኦ ያበረከቱን የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ቢሮ፣ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተባባሪ ዲን፣ የምርምር አቅራቢዎች እና ተሳታፊዎችን ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።

የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ዲን የሆኑት ዶ/ር ደረጄ ደምቤ  የቴማቲክ ምርምር በየሶስት አመት የሚጠናቀቅ ሲሆን የዲሲፒሊን ምርምር ደግሞ በየአመቱ የሚዘጋጅ መሆኑን አብራርተዋል። ይህ ግምገማም ያለቁ ምርምሮችን እንዴት እናስቀጥል እንዲሁም በሂደት ላይ የሚገኙትን ደግሞ ያሉበትን ሁኔታ ለማየት ይረዳል ብለዋል። ህብረተሰቡም ተጠቃሚ በሚሆንበት ሁኔታ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናና ድጋፍ ለማዘጋጀት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በኮሌጁ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ግዛቸው ኃ/ገብርኤል እንደገለጹት በወርክሾፑ ላይ የሚቀርቡ የምርምር ስራዎች ችግር ፈቺነታቸው፣ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚኖራቸው ጠቀሜታ፣ እንዲሁም ተደራሽነታቸው በጥልቀት እንደሚታይና የተለዩ ችግሮች ላይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ እና የሚገኙ ግኝቶችም ለመንግስት እንደ ፖሊሲ ግብዓትም ሊውሉ እንደሚችሉ ገልጸዋል። ግምገማው ቀጥሎ ሲውል የዲሲፕሊን ተመራማሪዎች የምርምር ስራዎቻችውን የሚያቀርቡ ይሆናል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et