የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ ፕሮጀክት ባከናወናቸው የተለያዩ ስራዎች ዙሪያ እና የተጠናቀቁ መልካም ተሞክሮዎች በቀጣይ የሚሰፉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር የካቲት 19 ቀን 2013 ዓ.ም በሀዋሳ ሀይሌ ሪዞርት የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል፡፡
በዚህን ወቅት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በፕሮግራሙ መክፈቻ ፕሮጀክቱ በደቡብና ሲዳማ ክልል ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በ6 ወረዳዎች እንዲሁም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ደግሞ በ4 ወረዳዎች ለሚገኙ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ አርባ ቀበሌዎች በግብርናው ዘርፍ አርሶ አደሮቹ በምግብ ሰብል ራሳቸውን እንዲችሉ ምርታማ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የማሳደግ፣ የማላመድና የማሰራጨት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ቴዎድሮስ ተፈራ የሀገር አቀፍ ሪያላይዝ ፕሮግራም ኃላፊ እንደገለጹት ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ውስጥ በአምስት ክልሎች ማለትም በትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች ላይ ዘላቂ የኑሮ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምግብ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የስርዓተ-ምግብ ችግሮችን ለማስወገድ፣ አካታች እና የስራ ዕድልን በመፍጥር ሴቶችንና ወጣቶችን በማሳተፍና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እና ድጋፎችን በማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ በመሆኑ ውጤቱን በተጨባጭ ለማየት ተችሏል ብለዋል፡፡
ፕ/ር ተስፋዬ አበበ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ ክላስተር ኃላፊ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች በቦሎሶ ቦምቤ፣ ዊራና ዊራዲጆ፣ ቃጫቢራ፣ ሻሻጎ፣ ሲልጤ እና ቦና ዙሪያ ወረዳዎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በበቆሎ፣ ቦሎቅ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ ዳጉሳ፣ ድንች እና ጤፍ ዝርያዎች ላይ እንደስነምህዳሩ አይነት ጥናትና ምርምር በማድረግ የተሸሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮቹ እንዲደርሳቸው መደረጉን ገልጸዋል፡፡