በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ኮምፒዩቲሽናል ሳይንስ ኮሌጅ የእንስሳት ህክምና ፋካሊቲ የእንስሳት ህክምና ማስተማርያ ሆስፒታል አስገንብቶ ካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም ሊያስመርቅ ችሏል፡፡ በምረቃው ስነስርዓት ላይ የተገኙት የዩኒቨርስቲው
ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ እንደተናገሩት ዩኒቨርስቲው በሀገራችን ውስጥ ከሚገኙ የመንግስት አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መሆኑንና በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በቴክኖሎጂ ሽግግሩ ዘርፍ ትልቅ ለውጥ እያስመዘገበ እንዳለ ታውቋል። በዚህም መሰረት በሀገራችን በእንስሳት ህክምና ዘርፍ ያለውን የተማረ የሰው ኃይል እጥረት በመቀነስ ረገድ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዩኒቨርስቲው ልዩ ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ በጀት መድቦ የእንስሳት ህክምና ማስተማርያ ሆስፒታል ያስገነባ ሲሆን ለወደፊት በዚሁ ዘርፍ የሚታየውን የተማረ የሰው ኃይል እጥረት ይቀርፋል ብለው እንደሚያምኑ አክለው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሀገራችን በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም ደግሞ 10ኛ መሆኗን ጠቅሰው በዚህም አሁን የተገነባው ሆስፒታልና በዚሁ ሆስፒታል ሰልጥነው የሚወጡ ባለሙያዎች ሀገራችን ከዚህ ሀብት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ በማድረጉ ረገድ አይነተኛ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም ሲገልጹ ዩኒቨርስቲው የእንስሳት ግጦሽና የእንስሳት ፋካሊቲን በአንድነት አቀናጅቶ ኮሌጅ የማድረግ እቅድ እንዳለው ጠቁመው ሆስፒታሉ አዲስ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ መሟላት ያለባቸውንና በጨረታ ሂደት መጓተትም ሆነ በተለያየ ምክንያት እስካሁን ያልተሟሉ እቃዎችን በፍጥነት ለሟሟላት ቃል ገብተዋል። በንግግራቸው ማጠቃለያም ሆስፒታሉ የተገነባው ለማህበረሰቡ ግልጋሎት ለመስጠት ስለሆነ ህብረተሰቡ እንደ እራሱ ንብረት በማየት አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግለት ጥሪ አቅርበዋል።
የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ዘይቱ ጋሻው በበኩላቸው በኮሌጁ ውስጥ ከሚገኙ ት/ክፍሎችና ፋካሊቲዎች አንዱ የእንስሳት ህክምና ፋካሊቲ መሆኑን አንስተው በዚሁ ፋካሊቲ በሚገኙ ተመራማሪዎች አማካኝነትም ለሀገር ፋይዳ ያላቸው ምርምሮች እየተካሄዱ መሆኑንና ሆስፒታሉ መገንባቱ ምርምራቸውን በብዙ እንደሚደግፍ ገልጸዋል። ይህም ከዚህ በፊት እኚሁ ተመራማሪዎች ለምርምር ስራ እስከ አርሲ ነጌሌ ድረስ ያደርጉት የነበረውን ጉዞ ያስቀራል ያሉ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ፕሮፌሰሮች በዚሁ ፋካሊቲ ውስጥ እንደሚገኙም ገልጸው ከሁለት ወር በፊት በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ዙሪያ በሲዳማ ክልል በመዘዋወር ያለውን አቅም ምልከታ ማድረጋችውን አውስተዋል። ዩኒቨርሲቲዎች የፌዴራል መንግስት ተቋማት እንደመሆናቸው መጠን ፋካሊቲው ከሚገኝበት አካባቢ ባሻገር እስከ ቦረናና ጅግጅጋ ድረስ አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።
በፋካሊቲው መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ካሳሁን አስማረ የእንስሳት ህክምና ትምህርት ክፍል ከዛሬ 18 ዓመት በፊት መጀመሩንና በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወደ ፋካሊቲ ደረጃ መሸጋገሩን የገለጹ ሲሆን የሆስፒታሉ መከፈት በእውቀትና በስነምግባር የበቁ ባለሞያዎችን በማፍራት ሀገሪቱ ከዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል። ፋካሊቲው በሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በቂ ውጤት ያመጡትንና በዲፕሎማ ሁለት ነጥብና ከዚያ በላይ ያላቸውን ተማሪዎች ወስዶ በመጀመርያ ዲግሪ፣ እንዲሁም ሌሎች ተማሪዎችን ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ እያስተማረ እንደሚገኝ ገልጸው ለመንግስት መስሪያ ቤቶችም ሙያዊ ድጋፍን ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በመጨረሻም የሲዳማ ክልልን፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርን፣ እንዲሁም የቱላ ክፍለ ከተማንና የጨፌ ኮቲ ጀቤሳ ቀበሌን ወክለው በስነስርዓቱ ላይ የተሳተፉ የዘርፉ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የህብረተሰብ ክፍሎች የሆስፒታሉ መገንባት አይነተኛ ሚና እንዳለው ገልፀው በሚያስፈልገው ሁሉ ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። በምረቃ ስነስርአቱ ላይ የታደሙ ተሳታፊዎች በሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኙ ላይብረሪዎች፣ የተለያዩ ላብራቶሪዎች፣ ኮምፒውተሮች፣ አልትራሳውንድ፣ የእንስሳት ቀዶ ህክምና፣ የእንስሳት ማቆያና ሌሎች ክፍሎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።