ከኢትዮጵያ መንገዶች ባልስልጣንና ከተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን በመንገዱ ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በሀዋሳ ዪኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት በሀዋሳ ከተማ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከፍተኛ ሀላፊዎችን ጨምሮ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ኢንስትቲዩት፣ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ የጅማና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተገኙ ሲሆን ከእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲዎች ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
ምሁራኑ በሚያስተምሩበት ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ጊዜያቶች ያከናወኗቸውን ተግባራቶች እና ያመጧቸውን ለውጦች እንዲሁም በመማር ማስተማሩ ሂደት የነበሩትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ፈትሸው የደረሱበትን የጥናት ውጤት ያቀረቡ ሲሆን በጥናታቸውም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ቀና ትብብርና ያላሳለሰ ድጋፍ መኖር፣ የአስተማሪዎች ጥረትና ተነሳሽነት መኖር፣ ለምርቃት የበቁት ተማሪዎች በሙያቸው የበቁ ሆኖ መውጣት የነበሩ ጠንካራ ጎኖች ሆነው ተነስተዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥና ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገብ፤ የመምህራን እጥረት፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ እና ሌሎች በመማር ማስተማሩ ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ተመላክቷል ፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮርፖሬት አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ በቀለ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ከተጠቀሱት 7 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውል በመፈራረም የተማሪዎችን ሙሉ ወጭ በመሸፈን በተለያዩ የምህንድስና ሙያ ዘርፎች ተማሪዎችን በማስተርስ ፕሮግራም እንዲሰለጥኑ እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በዘንድሮው ዓመት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙትን ጨምሮ በጥቅሉ የ 5 ሺህ ተማሪዎችን ሙሉ ወጪ በመሸፈን እንዲሰለጥኑ አድርጓል ነው ያሉት፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ባለፉት አሥርት ዓመታት ላሰለጠናቸው ተማሪዎች ከ377 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በዘርፉ የሚያጋጥመውን ብቁ የሰው ኃይል እጥረት በመቅረፍና ዘርፉን በማዘመን አወንታዊ ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ ረገድ አስተዋፅዖው ከፍተኛ መሆኑ በግምገማው የተመላከተ ሲሆን ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡት ምሁራን በበኩላቸው ምህንድስና ለመንገዱ ዘርፍ ብሎም ለሀገር እድገት ሚናው የማይተካ መሆኑን በማንሳት በዘርፉ የበቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በበኩሉ ዩኒቨርሲቲዎች ዘርፉን ለማሳደግ የሚያከናውኗቸውን በጎ ተግባራቶች እንደሚያደንቅና ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል፡፡
በውይይቱ መጨረሻም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥምረታቸውን አጠናክረው በማስቀጠል ካለፈው በላቀ ሁኔታ መሥራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡