የኮሌጁ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በስኳር፣ ደም ግፊት እና ከመጠን ያለፈ ውፍረት ዙርያ የግንዛብ ማስጨበጫ እና የነጻ ምርመራ ፕሮግራም በታቦር ክ/ከተማ ቲቲሲ ጎዳና ላይ አዘጋጅቷል። በፕሮግራሙ ዙርያ
አስተያየታቸውን የሰጡት የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ረ/ፕሮፌሰር አለሙ ጣሚሶ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬቱ በዋናነት በማህበረሰቡ ውስጥ ጎልተው የሚታዩ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሔን ለማፈላለግ እየሰራ እንደሚኝ ገልፀዋል። በዚህም ረገድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቁጥር እየጨመሩ የመጡትን የስኳር፣ ደም ግፊት እና ከመጠን ያለፈ ውፍረት በሽታዎች ቀድሞ በመከላከል እንዲሁም ከተከሰቱ ወዲያ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ለማስረዳት የግንዛቤ ማስጨበጫ ፌስቲቫሉ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
ማህበረሰቡ እራሱን ከአልኮል፣ ጨው ከበዛባቸው ምግቦች፣ ስጋን እና ቅባታማ ምግቦችን አዘውትሮ ከመመገብ እራሱን እንዲጠብቅና የአካል ብቃት እንቅስቃሴንም ማዘውተር እንደሚገባው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በመጨረሻም በሽታው የተገኘባቸው ስዎች ደግሞ ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ ተገቢውን ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸውና በሀኪም የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ በአግባቡ መተግበር እንደሚጠበቅባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።