ኮሌጁ ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በኮቪድ-19 ምክንያት ከስድስት ወር በፊት መመረቅ የነበረባቸውን ተማሪዎችን ባስመረቀበት ወቅት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ይህን የምረቃ
ሥነ-ሥርዓት ልዩ የሚያደርገው ባልተጠበቀና ባልታሰበ ጊዜ ዓለምን ያስጨነቀው የኮሮና ወረርሽኝ በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ከባድ ጫና ያሳረፈበት ወቅት መሆኑን ተናግረው አሁንም ቢሆን ተገቢው ጥንቃቄ እንደሚሻ አስገንዝበዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ አክለው በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ዓለም አቀፋዊ ይዘታቸው ተጠብቆ በከፍተኛ ደረጃ እንዲካሄዱ በተመረጡ የትኩረት መስኮችና የልዕቀት ማዕከላት ልዩ አጽንኦት ተሰጥቶ በመሠራት ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ሞቱማ ቶሌራ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ኮሌጁ ከ40 ዓመታት በላይ በደንና በሌሎች የተፈጥሮ ሀብት መርሃ-ግብሮች በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሠልጠን ሀገሪቱ የምትፈልገውን ባለሞያ በማበርከት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልፀው በቀጣይም በደንና የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም የልዕቀት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል በተያዘው የትምህርት ዘመን ለመሥራት አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ዲኑ በአከባቢ ደንና አየር ንብረት ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበትም ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንና ከዕለቱ ተመራቂዎች መካከል 53% ሴቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፊዴሪ የአከባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃድ በየነ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የደን መመናመንንና የአየር ብክለትን ለመከላከል ተመራቂዎች የፈጠራ ችሎታችዉን በማከል ከሥራ ጠባቂነት በመላቀቅ በዘርፉ የተለያዩ ሥራዎችን በመፍጠር መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በመጨረሻም የክብር እንግዳው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ ችግኞችን በመትክልና በመንከባከብ እያደረጉ ያሉትን አርአያነት በመከተል ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋፅዖ ማበርከት እንደሚገባው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡