አብዛኛውን ጊዜ በተመራቂ ተማሪዎች የሚሰሩ የመመረቂያ ጽሁፎች፣ምርምሮችና ፕሮጀክቶች ለተማሪዎቹ ውጤት መመዘኛ ከመዋል አልፈው ለባለድርሻ አካላትና ተመልካች ዕይታ ቀርበው ሲታዩ ማየት ያልተለመደ ሲሆን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ
ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ዳይሬክተር ቢሮ አዘጋጅነት በተመራቂ ተማሪዎች የተሰሩና የተመረጡ የመመረቂያ ፕሮጀክቶች በታህሳስ27/2013ዓ.ም ለዕይታ ቀርበዋል፡፡
ዶ/ር ተስፋዬ ባዩ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ዳይሬክተር ቢሮ ዳይሬክተር እንደገለጹት ተማሪዎች የቀለም እና የተግባር ልምምድ ካደረጉ በኃላ በመጨረሻው አመት በካፕስቶን ፕሮጀክት በኩል የሚሰሩት የፕሮጀክት አይነት ተለይቶ በመምህራኖቻቸው የክትትልና እገዛ እንዲሁም አቅም በፈቀደ መጠን አስፈላጊው የገንዘብ ድጋፍ ከፕሮጀክቱ በማድረግ የተማሪዎቹ ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆን የተሰራ መሆኑን ገልጸው ከዚህ በፊትም በ2011ዓ.ም ስድስት ፕሮጀክቶች ተሰርተው ለባለድርሻ አካላት እንዲቀርቡ በማድረጋችን ከቀረቡት ፕሮጀክቶች ተገምግመው ሁለቱ ማለትም የቀበሌ አስተዳደር ስርዓት እና የቱሪዝም መስህብ ስርዓትን ለማዘመን የሚያስችል መተግበሪያ በባለድርሻ አካላት ተቀባይነት አግኝተው ወደተግባር በመግባት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም የሚሰሩት የምርምር ውጤቶች በትንሽ ዋጋ የሚሰሩ እና ወጪ ቆጣቢ ሲሆኑ ሲበላሹም ለመጠገን ብዙ ገንዘብ እንደማያስወጡ ይሄንን ተሞክሮ እያሳደግን ከመጣን በሀገር ደረጃ ከውጪ ገዝተን ለማምጣት የምንጠቀመውን የውጪ ምንዛሪም ይቀንስልናል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የመመረቂያ ፕሮጀክቶቱ ለዕይታ ቀርበው አስተያየትና ውይይት ከተደረገ በኃላ ፕሮጀክቱን ለሰሩት ተመራቂ ተማሪዎች የዕውቅና ሰርተፍኬት ሽልማት ተበርክቶላቸው ፕሮግራሙ መጠናቀቁ ታውቋል፡፡