በሀገራችን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሊሰሩና ሊተገበሩ ታቅደው ሳይቋጩ በንጥልጥል ከቀሩ በርካታ ጉዳዮች አንዱ የመማር ማስተማሩ ሂደት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ኮቪድ-19 ወረርሽኝን እየተከላከሉ
ከፍተኛ ትምህርትና ስልጠናን የማስቀጠል እና ተቋማትንም መልሶ በመክፈት የመማር ማስተማሩን ሂደት ማስቀጠል እንደሚቻል አቅጣጫ በማስቀመጡ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲም ወረርሽኙ ከተከሰተ በኃላ በ2012ዓ.ም ሁለተኛ ሴሚስተር ላይ ሳይማሩ ወደየቤታቸው የሄዱትን ተመራቂ ተማሪዎች ጥሪ አድርጎ ትምህርታቸውን እንዲያገባድዱ አድርጓል፡፡
የሴቶች ህጻናት ወጣቶችና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በታህሳስ21/2013ዓ፣ም ባዘጋጀው የተመራቂ ሴት ተማሪዎች ሽኝት ፕሮግራም ላይ የተገኙት ዶ/ር ፍስሃ ጌታቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት እነደተናገሩት የዛሬውን ፕሮግራም ለየት የሚያረገው በዩኒቨርሲቲያችን ውስጥ ያሉ የሴት ተማሪዎች ቁጥር ከዚህ ቀደም ከነበረው አድጎ ከ35% በላይ በመድረሱ እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ተቋርጦ ለተወሰኑ ወራቶች በመቆየቱ የምረቃው ጊዜም ተላልፎ እዚህ የደረሰ ሲሆን ይሄ ክስተትም በተማሪዎቻችን ላይ የሳይኮሎጂ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ተያያዥ ችግሮችና ጭንቀቶችንም ቢያስከትልም እንኳ ይሄንን ሁሉ ነገር ተቋቁማችሁ ለዚህ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ምህረት ገነነ የሴቶች ህጻናት ወጣቶችና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዛሬ ለሴት ተመራቂ ተማሪዎች ይሄንን ፕሮግራም ያዘጋጀነው ስትመጡ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለን እንደተቀበልናችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ ብለን ለመሸኘት፣ በትምህርት ቆይታችሁ ያሳያችሁትን ብቃት ከዚህ ስትወጡም በምትሄዱበት ሁሉ እንድትደግሙት አደራ ለማለት እና መልካሙን ሁሉ እንዲገጥማችሁ ለመመኘትም ነው ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙም ላይ ከዚህ በፊት በዩኒቨርሲቲው አብላጫ ውጤት አምጥተው የቀሩ ሴት መምህራን የህይወት ተሞክሯቸውን ያካፈሉ ሲሆን ከስምንት ኮሌጆችና አንድ ኢንስቲትዩት አብላጫ ውጤት አምጥተው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ለወጡ 27 ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡