በ26/03/13 ዓ.ም በተካሄደው የመስክ በዓል ላይ በወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ ማጃ እና በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ ባራሶ በተደረገው የመክፈቻ ንግግር ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር በተጓዳኝ ህ/ሰቡን በግብርና ዘርፍ የተሻለ የእህል ዘርና የከብት ዝርያ በማቅረብና በስልጠና በማገዝ ላይ እንደሚገኝ ተገልጾአል፡፡
እንደ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግ/ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ አገላለጽ የመስክ ጉብኝቱ በዓል ዓላማው በአርሶ አደሮች ዘንድ የተሠራውን ሥራ አይቶ ለመገምገም እና ተወያይቶ ከልምዱ ተግዳሮትን መለየትና መፈለግ ላይ ያተኩራል፡፡ በዚህ መሠረት በሠርቶ ማሳያና በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ያለው የተለያየ የስንዴ ዝርያ ምርት ከተጎበኘ በኋላ ዩኒቨርሲቲው በስንዴ ብቻ ሳይሆን በድንችና በከብት እርባታም ጭምር የተለያየ አቅርቦት በማድረግ ኑሮአቸው እንዲሻሻል እየሠራ መሆኑን አርሶ አደሮቹ የገለጹ ሲሆን አሁንም ከባህላዊ የአሠራር ሁኔታ ወጥተው ወደ ዘመናዊው የሚሻገሩበትን መንገድ በፈር ቀዳጅነት ዩኒቨርሲቲው እንዲያሳያቸው ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም አፈር ላይ የሚደረገው ጥናት በስፋት እንዲቀጥልና ኖራና የመሳሰሉት መድኃኒቶች በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብላቸው አሳስበዋል፡፡
የክልሉ እርሻና ተ/ሀ/ል/ቢ/ም/ሀላፊ አቶ ክፍሌ ሻሾ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲውንና ግምባር ቀደም ተሳታፊ አርሶ አደሮችን በማመስገን ህ/ሰቡ ንቁና ፈጣን ተሳታፊ በመሆን በራሱ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖም ለሰው ልጅ ለለውጥ የሚያስፈልገው እርዳታ ሳይሆን እገዛ መሆኑን በመግለጽ ህ/ሰቡ መንገዱን አሳዩን የሚል ደረጃ ላይ መድረስ እንዳለበት አስምረውበታል፡፡ አክለውም የአርሶ አደሩ ፍላጎት ምን አንደሆነ በጥናት በመለየት የወረዳው የመስኩ ሠራተኞች ስልጠና እንድናዘጋጅ ማቅረብ ዋነኛው ድርሻቸው መሆኑን በመግለጽ ዩኒቨርሲቲው ከክልሉ ጋር በመተባበር የምርምር ማዕከል በመክፈት ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡