የኮሮና ወረርሽኝን መከላከል߹ተግዳሮቶችን መሻገር߹እድሎችን ማስፋትና መጠቀም በሚል ርዕስ ውይይት ተካሄደ። የኮሮና ወረርሽኝ በዓለማችን ብሎም በሃገራችን ከተከሰተ ጀምሮ የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ߹ ዜጎችን ከአልጋ እያዋለ߹
የሃገራትን ኢኮኖሚ በማሽመድመድ እና በማህብረሰብ ላይ ዘርፈ ብዙ የጤና߹ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተግዳሮቶችን እያስከተለ ክትባቱም ከዛሬ ነገ ተገኘለት ሲባል እነሆ ከዛሬ ደርሷል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ከምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ችግሩን በመገንዘብ የኮሮና ወረርሽኝን መከላከል߹ተግዳሮቶችን መሻገር߹ እድሎችን ማስፋትና መጠቀም በሚል ርዕስ በሲዳማ ክልል በይርጋለም ከተማ በህዳር 19/2013ዓ.ም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
ዶ/ር ዳኜ ሽብሩ የማህበራዊ ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን የውይይቱ አላማ የኮሮና ወረርሽኝ በማህበረሰብ ላይ እያስከተለ ያለውን ዘርፈ ብዙ የጤና߹ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተግዳሮቶች ላይ ብቻ ሳንታጠር ወረርሽኙ ያመጣቸውን መልካም እድሎች እና የወደፊት ተስፋዎች በመገንዘብ߹ ወቅታዊ ችገሮችን በመቋቋም߹ መከላከል߹ መግታትና ከዚህ አልፎም በመቆጣጠር ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር ሲሆን እኛም እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በወረርሽኙ ዙሪያ ጥናትና ምርምር በማድረግ በመከላከል አይነተኛ ሚና መጫወት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ዶ/ር አያኖ በራሶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በመክፈቻ ንግግራቸው ወረርሽኙ ሃገራችን ባለፉት ዓመታት በሁሉም ሴክተር ያስመዘገበችውን የልማት ድሎች ሁሉ ፈተና ላይ የጣለ እና አሉታዊ ጫና ያሳደረ ሲሆን በተለይ መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን߹ ትምህርትን߹ ስርዓተ ምግብን እና መተዳደሪያን በእጅጉ መጉዳቱን ገልጸው ዩኒቨርሲቲውም ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ የወረርሽኙን አስከፊነት በመገንዘብ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና በአካባቢው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለወረርሽኙ የግንዛቤ ማስጨበጫ በአካል߹ በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ሬዲዮ߹ ዌብ ሳይትና ማህበራዊ ድረ-ገጾችን በመጠቀም ትምህርት መስጠት߹ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ማምረትና ማከፋፈል߹ የኮቪድ ምርመራና የተኝቶ ህክምና አገልግሎት መስጠት߹ ለአቅመ ደካሞችና ጎዳና ላይ ለሚኖሩ ወገኖች የተለያዩ ማዕድ የማጋራት ሥራዎችን እንዲሁም ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣት አርሶ አደሮች ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ገዝቶ በማበርከት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን ተናግረዋል፡፡
በዕለቱም ወረርሽኙን ለመከላከል የሀገር በቀል ዕውቀት߹ ልምድ߹ ተሞክሮ ምን እንደሚመስል߹ ስለ ወረርሽኙ በሳይንስ የተገኙ እውነታዎችና በምርምር ላይ ያሉ ክትባቶች߹ ወረርሽኙ እያስከተለው ስላለው ጉዳቶችና መልካም አጋጣሚዎች ዙሪያ በተለያዩ ምሁራኖች ጥናቶች የቀርቡ ሲሆን ተሳታፊዎችም ጥናቱ ላይ በመወያየትና ገንቢ አስተያየቶችን በመስጠት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡