የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በ2012 ዓ.ም ሲያስተምራቸው የነበሩትን የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ እና የሶስተኛ ድግሪ 4780 ተመራቂ ተማሪዎችን በነሐሴ 23/2012 ዓ.ም አስመረቋል፡፡ ዶ/ር አያኖ በራሶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በዕለቱ ተገኝተው
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ 10 ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የመሆን ራዕይ አንግቦ በመሥራት ላይ እንዳለ ገልጸው “ዩኒቨርሲቲው በ8 ኮሌጆች እና በ3 ኢንስትቲውቶች 102 የመጀመሪያ ድግሪ፣ 122 የሁለተኛ ድግሪ እና 21 የሶስተኛ ድግሪ ፕሮግራሞችን በመክፈት ከ43470 በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት በሰባት ካምፓሶች እያስተማረ የቆየ ሲሆን የዚህን ዓመት የመጀመሪያ ሴሚስተር የመማር ማስተማሩንና መደበኛ ሥራዎችን ወቅቱን እንደጠበቀ በስኬት ያጠናቀቅን ቢሆንም ሁለተኛው መንፈቀ ዓመት ከተጀመረ በኃላ ያልተጠበቀው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ምክንያት ከመጋቢት ወር ጀምሮ ለተማሪዎቻችን ደህንነት ሲባል የገጽ ለገጽ ትምህርት አሰጣጥ እንዲቋረጥ ተደርጎ ከዩኒቨርሲቲው በመውጣታቸው የዓመቱ አብዛኞቹ የመጀመሪያ ድግሪ ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ባለመጨረሳቸው ለምረቃ ባይደርሱም በዛሬው ዕለት 4780 የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ እና የሶስተኛ ድግሪ ተማሪዎች ይህንን አስቸጋሪ ወቅት አልፋችሁ ለዛሬዋ ቀን በመድረሳችሁ ተመራቂ ተማሪዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል፡፡
ዶ/ር አያኖ አክለውም “የዛሬዋ ተመራቂ ተማሪዎችም ወደፊት የሚያጋጥማችሁን ተግዳሮቶች ተቋቁማችሁ ላጋጠመንም ጊዜያዊ ችግር መፍትሄን በመሻት፣ ሙስናና አድሎአዊነትን በመጠየፍ፣ በሀገራዊ አንድነትና በወንድማማችነት በመቆራኘት ያስተማራችሁን ህብረተሰብ በታማኝነት በማገልገል ሀገራችን ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ በመደገፍ የድርሻችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ” ብለዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው “የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ እና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ በዓለማችንና በሀገራችን ላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከፍተኛ ጫና ባደረሰበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ተመራቂዎች እልህ አስጨራሽ ጥረት አድርጋችሁ ለዚህ ዕለት መብቃታችሁ እጅግ የሚያኮራ ስኬት ሲሆን ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲም በዚህ የተደራረበ ጫና ባለበት ወቅት የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራውን አጠንክሮ በመቀጠል ለአንድ ሃገር ዕድገትና ብልጽግና ከምንም በላይ እውቀት እና ክህሎት እንዲሁም በመልካም አስተሳሰብና በውጤታማነት የተገነባ የሰው ሀብት ማፍራት እጅግ ወሳኝ እንደሆነ በመረዳት እንደ ሀገር ሌሎች የዓለም ሀገራት ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ ለመድረስ በምናደርገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የሙያ መስኮች በርካታ ምሁራንን በጥራት በማፍራት እየተወጣ ያለው ተቋማዊ ኃላፊነት እጅግ የሚያኮራና ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ ለዚህ ስኬታችሁ የዩኒቨርሲቲውን አመራሮች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ማድነቅና ማመስገን እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡
አቶ ጥራቱ አክለውም “ለሁላችንም የምትመች ሀገር መፍጠር የሚቻለው ሰው በሰውነቱ ብቻ የሀሳብ ነጻነቱ ተከብሮለት፣ በኃይማኖቱ፣ በብሄሩ ልዩነት ሳይደረግበት፣ በዕውቀቱ፣ በክህሎቱና በሀብቱ በመጥቀም በሀገሩ ተዘዋውሮና ተንቀሳቅሶ መሥራት የሚችልበት ሰላሟ የተጠበቀ ሀገር መገንባት ስንችል በመሆኑ የዛሬም ተመራቂዎች ሀገራችን እያጋጠማት ካለው የሰላም መደፍረስና አለመረጋጋት በፍጥነት ለመውጣት የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡና በምትሄዱበት ቦታና በምትሰማሩበት የሥራ መስክ ሁሉ ብልሹ አሠራሮችን በመጸየፍ፤ አብሮነትን፣ አንድነትን፣ ፍቅርና ሰላምን በመስበክ ዕውቀታችሁን ለሀገር፣ ለበጎ ሥራና ለችግር መፍቻ በማዋል የጋራ ቤታችን የሆነችውን ሀገራችሁን እንድትገነቡ አደራ እላለሁ” ብለዋል፡፡