በደቡብ ብ/ብ/ህ/ክልል እና በሲዳማ ክልል በኃላፊነት ላይ ላሉ ከፍተኛ ሴት አመራሮች በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአመራር አቅም ግንባታ ስልጠና ከነሐሴ 8-10/2012ዓ.ም ድረስ ተሰጠ፡፡
ዶ/ር አያኖ በራሶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በሀገራችን የሴቶችን ሁለንትናዊ አቅም በመጠቀም ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ በመሆኑ እንደሀገር ግማሽ ፐርሰንት የሀገሪቷ ካቢኒዎች ሴቶች መሆናቸው ትልቅ እምርታ እያመጣ መሆኑን ገልጸው በሀገራችን ሴት አመራር መሆን ብቻ ሳይሆን እዚህ ደረጃ ለመድረስ ከፍተኛ ትግል ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ዶ/ር አያኖ ቀጥለውም በሀገራችን በተለይ በገጠር አካባቢ በኢኮኖሚ፣የጋብቻ ጠለፋ ፣የቤት ውስጥ የስራ ጫና እና የተለያዩ ምክንያቶች ሴቶች ከወንዶች እኩል ዕድል እንደማይሰጣቸው እና ሴቶች በተለይ አመራር ላይ ያሉ በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት ስለሚረዱ ወደስራው አለም ሲቀላቀሉ አቅደው መንቀሳቀስ እንዲሁም የስራውን ወጤት መመዘንና መገምገም እናዳለባቸው ተናግረው ዩኒቨርሲቲው የሴት ተማሪዎችን ከመደገፍ አኳያ ከንጽህና መስጫ ጀምሮ ተጨማሪ የትምህርት ክፍለ ጊዜ በመስጠት ጭምር የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ቢሆንም ሴቶችን ለማብቃት ከስር ጀምሮ መሰራት ስላለበት ሰልጣኝ አመራሮች ይሄንን ለመቅረፍ በርትተው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በስልጠናውም ላይ አመራርና ውሳኔ ሰጭነት፣አመራርና ተግባቦት እንዲሁም እቅድ ክትትልና ግምገማ በሚል ርዕስ ሰልጣኞች ስልጠና መውሰዳቸው ታውቋል፡፡