የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ፕሮግራም ለሶስተኛ ጊዜ ተደረገ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ፕሮግራም ለሶስተኛ ጊዜ  በሲዳማ ክልል ቦርቻ ወረዳ በነሐሴ 8/2012ዓ.ም አደረገ፡፡

ዶ/ር አያኖ በራሶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በዕለቱ ተገኝተው እንደሀገር በዚህ ዓመት  አምስት ቢሊየን ችግኞችን  ለመትከል ዕቅድ የተያዘ ሲሆን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲም ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢና በወንዶገነት በርካታ አገር በቀል ችግኞችን እና ለምግብነት የሚሆኑ አትክልቶችን የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ በማስተባበር ለመትከል መቻሉን አስታውሰው የዛሬውም ችግኝ ተከላ ለሶስተኛ ጊዜ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር አያኖ በዛሬውም ዕለት በቦርቻ ለአካባቢ ጥበቃ የሚረዱ እና የአፈር መሸርሸርን ለማሰቀረት የሚያስችሉ ችግኞችን እና የፍራፍሬ ተክሎችን መትከል መቻሉን ገልጸው ቦታው ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር እንዳለበትና ከቦታውም በጎርፍ ታጥቦ የሚሄደው አፈር በደለል መልክ ወደ ሀዋሳ ሐይቅ በመግባት ሐይቁን ለከባድ አደጋ መዳረጉን  ከሁለት ዓመት በፊት በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች በጥናትና በምርምር  ሊታወቅ በመቻሉ አካባቢውን ለመታደግ በተደረገው ጥረትና እርብርብ አመርቂ ለወጥ መምጣቱን ገልጸው ይህንን ችግር ለመቅረፍ  እየሰሩ ያሉትን የዩኒቨርሲቲውን ተመራማሪዎች አመስግነው ቦታውም ለወደፊት ለምርምርና ሰርቶ ማሳያ ተሞክሮ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ሙሉጌታ ዳዲ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ምርምር ማዕከል በኩል ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር የሀዋሳ ሐይቅ ከፍተኛ ደለል እየሞላው በመሆኑ እና በሐይቁ ውስጥ ያሉ ብዘሃ-ህይወትንም ለመታደግ የችግሩን ምንጭ ስንፈትሽ ከዚህ አካባቢ የሚሄደው ጎርፍና አፈር ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ጎርፉን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት የአካባቢውን ማህበረሰብም ስልጠና በመስጠትና በማሳተፍ በሰራነው ስራ ውጤታማ መሆን የቻልን ሲሆን ታጥቦ የሚሄደውን አፈርም በተለያየ ደረጃና ቦታ ማስቀረት በመቻላችን  ተፈጥሮአዊ  በሆነ ዘዴ የተለያዩ የሳር ዝርያዎችን ፣ዛፎችን እና ፍራፍሬዎችን  በመትከል ተመጋጋቢና ተደጋጋፊ ስራዎችን መስራታቸውን ገልጸዋል፡፡

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et