በሳውዝ ስታር ኢንተርናሽናል ሆቴል የተዘጋጀው ይኼው የፀረ ሱሰኝነት ንቅናቄ መድረክ የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ከመቋሚያ የማኀበረሰብ ልማት ድርጅት ፤ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ፤ሴቶች ሕፃናትና
ወጣቶች ሚኒስቴር ፤ እና ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር መሆኑን የመቋሚያ ማኀበረሰብ ልማት ድርጅት ተወካይ አቶ ኤልያስ ካላዩ ተናግረዋል፡፡ የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ ዩኒቨርሲቲዎችን መሰረት ያደረገ የፀረ ሱሰኝነት ማኀበረሰብ አቀፍ ንቅናቄን ለማጠናከርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በተለይም ወጣቱ ትውልድ ከሱስ ነፃ እንዲሆንና በሀገር ልማትና ዕድገት የበኩሉን እንዲወጣ ለማስቻል መሆኑን አቶ ኤልያስ አስገንዝበዋል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አየለ አዳቶ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ከ43ሺ በላይ ወጣት ተማሪዎችን ከሁሉም የሀገሪቷ አከባቢዎች ተቀብሎ በተለያዩ ፕሮግራሞች በማስተማር ላይ መሆኑን ገልፀው እየተስፋፋ የመጣውን የአደገኛ ሱሶችና መድኃንቶች ዝውውር ሰለባ እንዳይሆኑ ግንዛቤ እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ራሳቸውን ከማንኛውም ሱስ ከሚያስይዙ ነግሮች በመራቅ ተምረው ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዲሆኑ መጠነ ሰፍ የግንዛቤ መስጨበጫ መድረኮች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ገልፀው በቀጣይነትም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በጉዳዩ ላይ በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለአንድ ቀን በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ከ80 በላይ የሚሆኑ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሁሉም ካምፓሶች ተወካዮች፤ ሀዋሳ ከተማ የሕግ አስከባሪዎች፤ የክበብ አባላትና የወጣቶች ተወካዮች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡
በፕሮግራሙ ፍፃሜ “ከሱስ ነፃ የሆነ ዩኒቨርሲቲ” የሚል ቢል ቦርድ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መግቢያ በር ላይ በአስተባባሪ ኮሚቴው ተተክሏል፡፡