የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ከዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ጋር ጳጉሜ 1/2016 ዓም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ትውውቅ አድርገዋል::

በመድረኩ የተገኙት የዩኒቨርሲቲውን ም/ፕሬዝዳንቶች፣ የኮሌጅ ዲኞች፣ ዳይሬክተሮች፣ ስራ አስፈጻሚዎች፣ ትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ አስተባባሪዎችና ቡድን መሪዎችን ያካተተው ካውንስል አባላት ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ስለነበራቸው ትጋትና ያልተቆጠበ አገልግሎታቸው አመስግነው ለአዲሱ ፕሬዝዳንት የመልካም የሥራ ዘመን ምኞታቸውን ገልፀዋል::

በመድረኩ ከትምህርት ሚኒስቴር የመጡ ተወካዮች እንደሀገር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እየተካሄደ ስላለው ሪፎርም አጠር ያለ ገለፃ አድርገዋል::

በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የመምህራን ልማት ዴስክ ኃላፊው አቶ በየነ ተዘራ እንዳሉት ትምህርት ሚኒስቴር ባለፉት ሁለት አመታት ሲያከናውን ከነበረው ሰፋፊ ሀገራዊ የሪፎርም ስራዎች መካከል የተቋማትን አለምአቀፋዊነት በሁሉም ዘርፍ ለማረጋገጥ ከአመራር እስከ አሰራር ያሉ ስራዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል። ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በትምህርት፣ አስተዳደርና አመራር ጥራት ላይ አዎንታዊ ለውጥ ያመጣሉ ያላቸውን የሪፎርም አቅጣጫዎች አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ በየነ ይህን ለማስፈጸም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ስምንት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የከፍተኛ አመራር ቅየራ መደረጉን ተናግረዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ከበደ ግዛው በበኩላቸው በሃገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ በተካሄደ ግምገማ ከተለዩ ችግሮች መካከል አመራሮች የአካባቢው ተወላጆች ብቻ እንዲሆኑ መደረጉ ያስከተለው አሉታዊ ተፅዕኖ በመኖሩ ተቋማቱን እንዲመሩ ኃላፊነት የሚሰጠው ብቃትን ብቻ መሰረት አድርጎ ዓለምአቀፋዊ አመለካከት እንዲኖር ለማስቻል የአመራር አደረጃጀትና ስብጥሩ በችሎታና ተገቢነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ከካውንስል አባላት ጋር ከተዋወቁ በኃላ እንደተናገሩት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ካሉ ትልልቅ ስራዎችን እየሰሩ ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው በዚህ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ሁሉም የአስተዳደርና አካዳሚክ ባለሙያዎች እንዲሁም የአመራሩ ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ገልፀዋል። ፕሬዚደንቱ አክለውም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑና በቅርብ ጊዜ ራስ-ገዝ እንዲሆኑ ከተለዩ ተቋማት ውስጥ መመደቡን አስታውሰው ይህንን ዕቅድ እውን ለማድረግና ሌሎች የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን ከዳር ለማድረስ የካውንስሉ አባላት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም ለአዲሱ ፕሬዝዳንት አቀባበል ታስቦ የተዘጋጀው በሲዳማ ባህል የአንድነትና የቃል ኪዳን መገለጫ የሆነው ሻፌታ ቀርቦ የትውውቅ መርሃግብሩ ተጠናቋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et