የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ አዲስ ለተመደቡት ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ የስራ ርክክብ አደረጉ::

በኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮችና በዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አባላት ትውውቅ በተጀመረው የሥራ ርክክብ ስነ ሥርዓት ላይ የአካዳሚክ ጉዳዮች፣ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር እና የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚደንቶች በየዘርፉ የያዙትን የ2017 በጀት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዶች እንዲሁም ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች አስመልክቶ ገለፃ አድርገዋል:: ምክትል ፕሬዝዳንቶቹ ዶ/ር ኢ/ር ፍስሃ ጌታቸው፣ ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ እና ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን አሁናዊ ቁመና፣ ዕድሎችና ፈተናዎች በየዘርፋቸው ለይተው አብራርተዋል።

የቀድሞው ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በርክክቡ ወቅት ባደረጉት ንግግር በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪነት ጀምረው በቦርድ አባልነት፣ በመምህርነት፣ በቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝዳንትነት፣ በአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንትነት እና በፕሬዝዳንትነት ለበርካታ ዓመታት በማገልገል በሕይወት ዘመናቸው አብዛኛውን ግዜ እንዳሳለፉበትና በርካታ ትምህርትና ልምድ የቀሰሙበት መሆኑን አንስተው ተቋሙ ከምንም በላይ በሕይወታቸው ልዩ ትርጉም እንደሚሰጣቸው ገልፀዋል:: ዶ/ር አያኖ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሀገራችን ከሚገኙ ጠንካራ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቁንጮነት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቁመው ይህ ሊሆን የቻለው ከአስተዳደር ሰራተኞች ጀምሮ፣ በመምህራንና ተመራማሪዎች፣ በተማሪዎች፣ በአጋር አካላትና በመላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት የጋራ ትብብር በመሆኑ በኃላፊነት ዘመናቸው በክብርና በፍቅር አብረዋቸው የሰሩትን በሙሉ አመስግነዋል። በመጨረሻም አዲስ ለተሾሙት ፕሬዚደንት መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው ምኞታቸውን ባስተላለፉበት ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲውን ወደላቀ ከፍታ ለማሸጋገር ሁሉም ሰራተኞች ከፕሬዚደንቱ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

አዲሱ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በበኩላቸው የቀድሞው ፕሬዚደንት በነበራቸው የአመራርነት ዘመን ዩኒቨርሲቲውን እንደ ሀገር በመልካም ጎኑ የሚያስጠራ ስራ መስራታቸውንና ለዚህም ምስጋና እንደሚገባቸው ተናግረዋል። እሳቸው ወደ ኃላፊነት የመጡበት ጊዜም እጅግ ወሳኝና አጠቃላይ ተቋማዊ የራስ-ገዝነት ሽግግር እየተካሄደ የሚገኝበት በመሆኑ በውስጡ በርካታ እድሎችና ፈተናዎችን የያዘ እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ችሮታው በሁሉም ዘርፎች ላይ አዎንታዊ ውጤት ለማምጣት በመተማመን ላይ መመስረትና ተናቦ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመጨረሻም ፕሬዝዳንቶቹ የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ርክክብ ካደረጉ በኃላ በማኔጅመንት አባላት ታጅበው የዋናው ግቢ ገፅታን ጎብኝተዋል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et