ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት ሀገራችን ወደ መካከለኛ ገቢ ሃገራት ጎራ ለመቀላቀል በምታደርገው ጉዞ የግብርናው ዘርፍ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ አጋዥ መሆን እንዳለበትና ግብርናው ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ሲችል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ደግሞ የቴክኖሎጂ ሽግግር ግብዓት ተጠቅሞ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን የመተካት ሚና እንዲሁም የውጭ ገቢ ለማስገኘት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል:: በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ዋነኛው የትኩረት መስኩ አድርጎ ከለየው ግብርና ዘርፍ ጋር ጥብቅ ትስስር ባለው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ጋር በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል:: በዚህም የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሞዴል አምራች እንዲሆን ለማስቻል ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እንደ ቁልፍ ባለድርሻ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል::
የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኃይሉ ዬቴራ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከኮርፖሬሽኑ ጋር በቅርበት ለመስራት ያሳየውን ቁርጠኝነትና እስካሁንም እያደረገ ላለው አስተዋፅኦ አመስግነው በተለይም የይርጋለም አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተረፈምርት አያያዝ ላይ ያጋጠመውን ክፍተት በእውቀትና ቴክኖሎጂ እገዛ ለማድረግ እንዲሁም ተጨማሪ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በጋራ ለመስራት ትብብሩ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል:: ፓርኩ ለየት የሚያደርገው ሁሉንም የማምረቻ ግብዓቶቹን የሚወስደው ከግብርናው ዘርፍ መሆኑን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በቡና: አቦካዶ: ወተት: ቲማቲም: እና ሌሎች የግብርና ምርቶች ፍሳሽ ተረፈ ምርቶችን ለማስወገድ የሚያገለግሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል:: ነገር ግን አሁን የቅድሚያ ቅድሚያ ሥራ የሚፈልገው ደረቅ ቆሻሻን (ተረፈ ምርትን) ወደ ጠቃሚ ሀብቶች የመቀየር ቴክኖሎጂና እውቀት እንደመሆኑ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ሰፊ ትብብር ለማድረግ ማስፈለጉን ገልፀዋል::