ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በትብብር ሊሰራ ነው።

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና ከይርጋለም የተቀናጀ አግሮኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር በፓርኮቹ እድልና ፈተናዎች፣ በምርምርና ጥናት እንዲሁም የተረፈ ምርት አጠቃቀም ላይ በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተወያይቷል።

የም/ቴ/ሽ/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ መድረኩን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በ2022 ዓ.ም መካከለኛ ገቢ ካላቸው የአለም ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ስድስት ዘርፎችን በመለየት ወደ ሥራ መግባቷን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር በትብብር እንዲሰሩ አዋጅ እንደጸደቀ ገልፀው የመንግስት ልማት ድርጅቶችም ከአመታዊ በጀታቸው 0.2% የሚሆነውን ለዚሁ ስራ እንዲመድቡ ደንብ መዘጋጀቱን አስታውሰዋል። በዚህ መነሻነት ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በምርምር: በማማከር: በእውቀት ሽግግር እና ሌሎች ዘርፎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር በትብብር ሲሰራ መቆየቱን የጠቆሙት ም/ፕሬዚደንቱ የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አመራሮችና አጋር አካላት ተቋማዊ ትስስርና ትብብር በመመስረት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ለመስራት መምጣታቸውን አድንቀው ሁሉም የየድርሻቸውን ኃላፊነት ለመወጣትና ውስን የሆነውን የሀገር ሀብት አቀናጅተው የተሻለች ሀገር ለመፍጠር መረባረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል::

የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሉ ዬቴራ በበኩላቸው የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአሁኑ ሰዓት 24 ባለሀብቶችንና 28 ፕሮጀክቶች ይዞ በስራ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው የልማት ዕድል የራሱ ፈተናዎች ያሉት እንደመሆኑ በተለይ የተረፈምርት አያያዝ ላይ ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ ሣይንሳዊ መፍትሄ እንዲያቀርብላቸው ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል:: አቶ ኃይሉ አክለውም ፈጣን መፍትሄ ከሚፈልጉ ተግዳሮቶች አንዱ የአቮካዶ ዘይት ማምረቻ ተረፈምርት አያያዝና አጠቃቀም መሆኑን ጠቅሰው ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በይበልጥ ለመስራት የተበታተኑ ጥረቶችን በማሰባሰብ የተሻለ መግባባት ላይ መድረስ ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የተለያዩ የአቮካዶ ተረፈምርትን ወደ ተሻለ ጠቃሚ ሀብት ለመቀየር ያስችላሉ የተባሉ ጥናታዊ ጽሁፎችና ወደ ተግባር ጭምር የተቀየሩ የተረፈምርት ውጤቶች ከግብርና ኮሌጅ: ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት: ከደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ በተውጣጡ መምህራንና ተመራማሪዎች ለውይይት ቀርበዋል:: በቀረቡት የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ሰፊ ውይይት ከተካሄደ በኃላ ተቋማቱ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲቻል ተበታትነው የተሰሩትን ሙከራዎች በማቀናጀት ችግሩን ወደ መልካም ዕድል ለመለወጥ ስምምነት በመፈረም ትብብሩን እንደሚያጠናክሩ ገልፀዋል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et