ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ዕውቀት ሽግግር፣ በሰው ኃይል አቅምና መሠረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም ተያያዥ የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ነሐሴ 9/2016 ዓም በአዲስ አበባ ተፈራርሟል፡፡
ከሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ስምምነት የተፈራረሙት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ወርቁ ጋቸና እንዳሉት የስማርት ሀገር ግንባታ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና የጎላ በመሆኑ የስምምነት ማዕቀፉ በኢንስቲትዩቱ የሚሰሩ የሰዉ ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ዉጤቶችን ለዩኒቨርሲቲዎቹ ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል፡፡ በተጨማሪም የተቋማቱን አሰራር ለማዘመን መሰረት የሚጥል መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱን ከኢንስቲትዩቱ ጋር የተፈራረሙት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በበኩላቸዉ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዓላማዎች አንዱ የምርምር ስራ መሆኑን ገልፀው ይህንን ስራ በቴክኖሎጂ በመደገፍ የበለጠ ዉጤታማ ለማድረግ ከኢንስቲትዩቱ ጋር የሚደረግ ቅንጅት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ አክለዉም ከኢንስቲትዩቱ በጋራ በመሆን በተማሪዎች ላይ የሚስተዋለዉን ቴክኖሎጂ-ነክ የዕዉቀትና ክህሎት ክፍተቶች ለመሙላት እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡