ሀዩ የካንሰር ህክምና ማዕከል አስመረቀ

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የካንሰር ህክምና ማዕከል እና ሌሎች የጤና አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ዛሬ አስመረቀ::

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር በከፍተኛ ወጪ ያስገነባቸውን የካንሰር ህክምና ማዕከል እና ሌሎች በዘመኑ ቴክኖሎጂ የተደራጁ አምስት ከፍተኛ የህክምና አገልግሎቶች መስጫ ማዕከላትን የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር እና የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ አስመርቋል።

ዛሬ የተመረቁት የህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የካንሰር ጨረር ህክምና ማዕከል፤ የፎረንስሲክ እና ስነ-ምረዛ አገልግሎት፤ ሞዴል የህዝብ መድሐኒት ቤት፤ የጨቅላ ህፃናት ፅኑ ህክምናና ልህቀት ማዕከል እና የስነ-አዕምሮ ህክምና አገልግሎት ማዕከል ሲሆኑ በተለይም የካንሰር ሕክምና እና የፎረንስክ ምርመራ ማዕከል በርካታ ዜጎች አዲስ አበባ ወይም ከሀገር ውጪ ካልሄዱ አገልግሎት ማግኘት ስለማይችል ለብዙ እንግልትና ወጪ ሲዳረግባቸው የነበሩ እንደሆነ ተገልፅዋል::

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር በተጓዳኝ የምርምር ፤ የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስረፅ በመንግስት የተጣለበትን ተልዕኮ እየተወጣ እንደሆነና በዚህ አንፃርም የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ የጤና ባለሞያዎችን ከማፍራት ባሻገር በሲዳማና አጎራባች ክልሎች ለሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች አቅምን ያገናዘበና ደረጃውን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት በተለይም በአጥንት ፤ በጨቅላ ህፃናት፤ ድንገተኛ አደጋ፤ በአይን፤ በልብና ከአንገት በላይ እንዲሁም በከፍተኛ የቀዶ ጥገና ሕክምና ዘርፎች ከፍተኛ አስተዋፆ እያበረከተ ነው፡፡

የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው የካንሰር ህክምና ማዕከሉ ስራ መጀመር በሀገራችን በአሁን ወቅት በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ የጤና ችግሮች ባለበት ለማስቆምና አክሞ ለማዳን መንግስት ያስቀመጠውን የጤና ፖሊሲ አቅጣጫ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጎላ አስተዋጾ እያበረከተ ነው ብለዋል:: የጨቅላ ሕፃናትን መጠነ ሞት እና መቀንጨር ለመከላከል የሚረዳውን የህክምናና ልህቀት ማዕከል ማደራጀቱም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጤናው አገልግሎት ዘርፍ ታላቅ ሃገራዊ አስተዋፅኦ እያደረገ ለመሆኑ ተጨማሪ ማሳያ መሆኑን ዶ/ር ደረጄ አክለዋል::

የሲዳማ ብ/ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር በየነ በራሳ ባስተላለፉት መልዕክት የህብረተሰብን ችግር ከግንዛቤ በማስገባት የተጠኑና ደረጃቸውን የጠበቁ እነዚህ የህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን መገንባት ብሎም ለማህበረሰቡ በቅርበትና በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ በማድረግ ሀዋሳ ከተማን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ማዕከል በማድረግ ረገድ የመንግስትን የሪፎርም አቅጣጫ በመፈፀም ዩኒቨርሲቲው ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን አድንቀዋል:: ም/ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ የተመረቁት የህክምና መስጫ ማዕከላት በውስጣቸው የያዙት የቴክኖሎጂ ግብዓቶች በርካታ መዋዕለ ነዋይ የፈሰሰባቸው የሀገርና የሁሉም ዜጋ አይተኬ ሀብት በመሆናቸው ሁሉም የሚመለከተው ባለድርሻ አካልና የተቋሙ ሀላፊዎች በየደረጃው ያሉ ባለሞያዎች ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥበቃ እንዲያደርጉላቸው በአፅኖት አሳስበዋል፡፡

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et