ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢኖቬሽንና ቴከኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢኖቬሽንና ቴከኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የኢኖቬሽን እና ስታርታፖችን የመደገፍ ብሎም ምቹ ስነ-ምህዳር ለመፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች በትብብር ለማከናወን የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ግንቦት 16/2016 ዓ.ም ተፈራርሟል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከድሬዳዋ፣ ጅማ እና ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተደረገው የጋራ መግባቢያ ስምምነት ፊርማ ስነስርዓት ላይ እንደገለፁት ስምምነቱን በኢኖቪዝ-ኬ ኢንኩቤሽን ማዕከል እና በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ አቅሞችን አቀናጅቶ በመጠቀም በዘርፉ ውጤት ለማምጣት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን በመወከል ስምምነቱን የተፈራረሙት የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዮስ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የፈጠራ፣ የምርምር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን ለመስራት ያለውን ከፍተኛ ፍላጎትና እምቅ አቅም ጠቅሰው ይህን መሰል ቅንጅት መፈጠሩ እንደሀገር ያሉ አቅሞች እንዳይባክኑ ያደርጋል ብለዋል።