10ኛው ዙር ብሔራዊ የበጎ ፍቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ስልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተከናወነ።
የኢፌዲሪ ሰላም ሚኒስቴር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተውጣጡ 2000 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አምባሳደሮችን ለ33 ቀናት የሚቆይ የ10ኛ ዙር ስልጠና ለመስጠት የተቀበለ ሲሆን የስልጠናው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የሰላም ሚኒስቴር፣ የሲዳማ ብሔራዊ ክልል እንዲሁም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና አጠቃላይ ማህበረሰብ በተሳተፉበት ዛሬ በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተከናውኗል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ተወካይና የአስ/ል/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ ሰልጣኞችን በሀገር አቀፍ ደረጃ በሰላማዊነቱ ወደሚታወቀው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት ሰላም ለአንድ አካል በኃላፊነት የሚተው ባለመሆኑ እንደእናንተ በበጎ ፈቃድ የሀገራችንን ሰላም ለማረጋገጥ አምባሳደር ሆነው ለማገልገል የሚወስኑ ብዙ ወጣቶች ያስፈልጉናል ብለዋል። ም/ፕሬዚደንቱ አክለውም ወጣቶች የነገው ሀገር ተረካቢ እንደመሆናችሁ የትኛውም ሰላምን ዋና መሳሪያ አድርጎ በማይጠቀም መንገድ ላይ በፍጹም ባለመሳተፍ ይልቅም ሰላምና ፍቅርን በመስበክ የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅና ሰላሟን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ የወጣቶች በጎ ፈቃድ ፕሮግራም መሪ ስራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ገመቺስ ኢትቻ የሰላም ሚኒስቴር ሰላም የብዙ ባለድርሻ አካላት የጋራ ስራ ውጤት መሆኑን በመገንዘብ በተለይም ወጣቶች ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ ትርክቶችን በመፍጠር ብሔራዊ መግባባት ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። "በጎነት ለአብሮነት" በሚል መሪ ሀሳብ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በዘጠኝ ተከታታይ ዙሮች ከ47 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን አሰልጥኖ በማስመረቅ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች አሰማርቶ ማህበራዊ ትስስርን በማሳደግ፣ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር እንዲሁም አጠቃላይ ዘላቂ ሰላምን ከመገንባት አንጻር ፍሬያማ ስራ መሰራቱን አቶ ገመቺስ ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ጃጎ አገኘሁ በበኩላቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝሃ ቋንቋ፣ ባህልና እሴት ባለባቸው ሀገሮች የጋራ መግባባትን ፈጥሮና በሰላም ተሳስሮ መኖር የምርጫ ሳይሆን የግዴታ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው ይህንኑ ለማረጋገጥ የዚህ ዙር ሰልጣኞች በስልጠናው የሚያገኙትን እውቀትና ክህሎት እንደ ስንቅ መጠቀም ይገባቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጲያ ወጣቶች ካውንስል ሰብሳቢ ወጣት ፉአድ ገና የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ለሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ በስብዕና የተገነቡ ሀገር ወዳድ ወጣቶችን ከመፍጠር አኳያ እየሰራቸው የሚገኙ ስራዎች እጅግ የሚደነቁ መሆኑን ገልፀው ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር እንደመሆኗ ይህን እምቅ ኃይልና የብሩህ አዕምሮ ባለቤትነትን የሚያላብስ የእድሜ ክልል በአግባቡ ክትትልና ድጋፍ ተደርጎለት እምርታዊ ለውጦችን የምናመጣበት በአግባቡ ካልተገራ ደግሞ ለጥፋትና ሁከት መሳሪያ ሊሆን ስለሚችል መሰል መድረኮች ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል::
የዕለቱ መርሐ ግብር በወሊማ ባህላዊ የትርኢትና ኪነት ቡድን የመድረክ ዝግጅቶች ደምቆ የተጀመረ ሲሆን በኢትዮጵያ ህዝብ ብሔራዊ መዝሙር ተደምድሟል።