በዳሌ ወረዳ በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች የተደረገ ድጋፍ የመስክ ምልከታና ውይይት ተካሄደ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም በሲዳማ ክልል ዳሌ ወረዳ ዱባ ቀበሌ በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች በተቀናጀ የአሳ፣ የዶሮና የጓሮ አትክልት ልማት ስራ የተደረገ ድጋፍ የመስክ ምልከታና የማህበረሰብ ውይይት ተካሂዷል።

የምርምርና ቴ/ሽ/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዮስ በዳሌ ወረዳ በዱባ ቀበሌ የተሰራው ስራ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት በክልሉ ባሉ ዘጠኝ ወረዳዎች በተቀናጀ የአሳ፣ የዶሮና የጓሮ አትክልት ልማት ከሚሰራው ስራ መካከል አንዱ መሆኑን ገልፀው ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማላመድ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን በማከናወን በክልሉ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የህብረተሰቡን ቾግር በመፍታት ገቢያቸዉ እንዲያድግና ኑሯቸዉ እንዲሻሻል እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተሩ አቶ ማርቆስ ፍስሀ በበኩላቸው ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ሥራ ላላገኙ የተደራጁ ወጣቶች የተደረገዉን ድጋፍ ለተሳታፊዎች በዝርዝር አቅርበዋል::

የሲዳማ ክልል እንስሳትና ዓሳ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ ጆምባ እንደገለፁት ክልሉ ጠባብ መሬት ያለበት በመሆኑ ህብረተሰባችን ባለው ጠባብ መሬት ላይ ብዙ ምርት የሚገኝበትን የዚህ መሰሉን የተቀናጀ የልማት ስራዎች መተግበር እንደሚገባዉ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተግባር አሳይቶናልና ዩኒቨርሲቲዉን በክልሉ ስም ላመሰግን እወዳለሁ ብለዋል።

የዳሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ ዮሴፍ ባስተላለፉት መልዕክት ዩኒቨርሲቲዉ የተለያዩ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን በወረዳዉ እየሰራ መሆኑን ገልፀዉ በተቀናጀ የዓሳ፣ የዶሮ እና የጓሮ አትክልት ልማት ስራዎች የተሰራው ሥራ ለአካባቢዉ ማህበረሰብ የሚጠቅምና ለሌሎችም ተሞክሮ የሚሆን በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዉን አመስግነዉ ህብረተሰቡም በአግባቡም ይህንን ተሞክሮ በደንብ አስፍቶ እንዲጠቀምበት አሳስበዋል።

በመጨረሻም በቀበሌው የተቀናጀ የዓሳ፣ ዶሮና የጓሮ አትክልት ልማት ስራዎች ያሉበት ሁኔታን ለመገምገም እንዲቻል የመስክ ምልከታ ከተካሄደ በኃላ በስራው ላይ ባጋጠሙ ተግዳሮቶችና ችግሮቹን ለመፍታት የተሰሩ ስራዎች ምን እንደሚመስሉ፣ ከባለድርሻ አካላት ምን እንደሚጠበቅ ከአርሶ አደሮች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተነሱ ሃሳቦች ላይ ከዩኒቨርሲቲውና የክልሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ዉይይት ተካሂዷል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et