ስለ ካፒታል ገበያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጠ::
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን (Ethiopian Capital Market Authority) እና የኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለንዋዮች ገበያ (Ethiopian Securities Exchange) በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ በመገኘት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለፃ ሰጥተዋል::
በፕሮግራሙ መግቢያ ላይ ይህን የመሰለ ለየት ያለ መድረክ በዩኒቨርሲቲያችን እንዲዘጋጅ ያደረጉትን አካላት በሙሉ ያመሰገኑት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር እንጅነር ፍስሃ ጌታቸው የሁለቱን ተቋማት ልዑካን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል:: ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የብዙሃን ተቋም እንደመሆኑ እዚህ የሚዘራ እውቀት ብዙ ሺዎች ጋር ተባዝቶ እንደሚደርስ ያብራሩት ም/ፕሬዚደንቱ ከፋይናንስ ሙያ ራቅ ያሉ ሰዎች ብዙም ስለማናውቀው ወቅታዊና አስፈላጊ ጉዳይ ግንዛቤ ማስጨበጥ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል::
በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ታዬ የተመራው የተቋሙ ልዑክ ስለ ካፒታል ገበያ እና የሰነደ መዋዕለንዋዮች ገበያ ምንነት: በሁለቱም ተቋማት የሚሰሩ ሥራዎች: አሰራሩን የሚደግፋ የህግ ማዕቀፎችና መመሪያዎች: ለግለሰብ: ተቋማት እና ሃገራት ኢኮኖሚ በካፒታል ገበያ የሚገኘው ትሩፋትና እድሎች በተለያዩ የስራ ኃላፊዎች ገለፃ የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊ የዩኒቨርሲቲያችን ማህበረሰብ አባላት ጥያቄዎች ተነስተው በዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል::
በመርሃግብሩ ማጠቃለያም ዶ/ር ብሩክ በተለይም ከዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መምህራንና ተማሪዎች ጋር ወደፊት የተለያዩ ስራዎችን ተቀራርቦ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል::