የእንስሳት ህክምና ት/ክፍል ነጻ የእንስሳት ህክምና አገልግሎት ሰጠ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ስር የሚገኘው የእንስሳት ህክምና ፋካሊቲ በዛሬው ዕለት በቱላ ክ/ከተማ ሆንሴ ሜዳ ጨፌ ኮቴጀቤሳ ቀበሌ የአርሶአደሮች መስክ ላይ ነጻ የእንስሳት ህክምና አገልግሎት ሰጥቷል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በመስኩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ላይ ፋካሊቲው በእንስሳት ህክምና ዘርፍ ብቁ ተማሪዎችን ለማስመረቅ የሚረዳውን በአስፈላጊ የመማሪያ ቁሳቁሶች የተደራጀ ዘመናዊ ሆስፒታል አስገንብቶ ለስራ ማብቃቱን አስታውሰው በዚህ ሆስፒታልም ለአካባቢው ማህበረሰብ የእንስሳት ህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ ገልፀዋል። ፕሬዚዳንቱ አክለውም ኮሌጁ ብቁ ተማሪዎችን ከማፍራት ጎንለጎን በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በሲዳማ ክልልና አከባቢው ከሚገኙ አርሶአደሮች ጋር በቅርበት ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል እንደዛሬው ፕሮግራም ያሉ ነጻ የእንስሳት ህክምና አገልግሎቶችን ማቅረብ ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል።
የእንስሳት ሕክምና ክፍል ኃላፊው ዶ/ር ምሻሞ ሱሌይማን በበኩላቸው የሆንሴ ሜዳ ጨፌ ቀበሌ ለአከባቢውና ለሀገር የሚተርፍ እምቅ የእንስሳት ሀብት አቅም ያለው መሆኑን በማንሳት በትብብር ከተሰራ ሀብቱን ለሀገር በሚጠቅም ደረጃ መጠቀም እንደሚቻል ተናግረዋል። ዶክተሩ ጨምረውም ፋካልቲው የመስክ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራውን ተማሪዎቹ እውቀታቸውን በተግባር-ተኮር ክህሎት የሚያሳድጉበትና በማህበረሰቡ ውስጥ ስለዘመናዊ የእንስሳት ህክምና ግንዛቤ የሚፈጥሩበት ዕድል አድርጎ እየተጠቀመው እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በቱላ ክ/ከተማ የእ/አ/ሀ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮናስ ዮሴፍ በቀጣይ በመንግሥት ደረጃ እንደሀገር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ያለውን "የሌማት ትሩፋት" እንቅስቃሴ ከግብ ለማድረስ የስጋና የወተት ተዋጽኦ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባና ይህንንም ስራ የእውቀትና የፈጠራ ማዕከላት ከሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን ማሳካት ይቻላል ብለዋል። ኃላፊው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ለህብረተሰቡ በማስተዋወቅ እንዲሁም የእንስሳት ህክምናን በመስጠት የማይተካ ሚና እየተጫወተ ስላለው ተግባር ቀበሌውን ወክለው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም የእንስሳት ህክምና አገልግሎቱን ያገኙ አርሶአደሮች ለተደረገላቸው ነገር ምስጋናቸውን ሲያቀርቡ፤ የህክምና አገልግሎቱን በመስጠት የተሳተፉ የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች ባደረጉት ተግባር መደሰታቸውንና መሰል የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያላቸውን ሀሳብ አካፍለዋል።