የአባወራው ጉዞ" ትያትር ለእይታ ቀረበ

የአባወራው ጉዞ" ትያትር ለሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እይታ ቀረበ::

በእውቁ አሜሪካዊ ፀሐፌ-ተውኔት አርተር ሚለር ተፅፎ በኢትዮጵያዊው አለማየሁ ገብረሕይወት የተተረጎመው "የአባወራው ጉዞ" ትያትር
ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት ላይ በሀዋሳ ዩንቨርሲቲ  ዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ለተማሪዎች እይታ ቀርቧል።

በተክሌ ደስታ አዘጋጅነት በቀረበው በዚህ ትያትር ላይ ተስፋዬ ገብረ ሃና፣ ሚካኤል ታምሬ፣ ሱራፌል ተካ፣ ብሩክ ምናሴ፣ ትግስት ባዩ፣ ገነት አሰፋ እና ሌሎች አንጋፋና ወጣት የኢትዮጵያ ተዋንያን ተሳትፈውበታል። ከ2 ሰዓት በላይ ርዝማኔ ያለውና በአንድ ቤተሰብ የሕይወት ውጣ ውረድ ላይ የሚያጠነጥን ታሪክ የያዘው ትያትሩ ለሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በነፃ ለእይታ እንዲቀርብ በአሜሪካ ኤምባሲ ድጋፍ የተደረገለት ሲሆን ፕሮግራሙን የሀዋሳ ዩንቨርሲቲ የውጭ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ከተማሪዎች ህብረት ጋር በመሆን አስተባብረውታል::

የውጭ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እመቤት በቀለ በፕሮግራሙ መዝጊያ ላይ ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እንዲህ አይነት በጎ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ የጥበብ ውጤቶች እያዝናኑ ቁምነገር የሚያስጨብጡ እንደመሆናቸው ለልጆቻችን ይሄንን ዕድል ይዘው የመጡትን አካላት በዩኒቨርሲቲው ስም ከልብ አመሰግናለሁ ብለዋል:: በትያትሩ ላይ የተሳተፉትን ሁሉንም አባላት እንዲሁም የአሜሪካ ኢምባሲን ይሄን መርሃግብር በማዘጋጀታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

ትያትሩ ላይ በትርጉም ስራ እንዲሁም በትወና የተሳተፈው አለማየሁ ገብረህይወት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች እንዲሁም ተማሪዎች ዝግጅቱ ውጤታማ እንዲሆን ላደረጉት ቀና ትብብር እና ለሰጡት ፍቅር ምስጋና በማቅረብ ለቀጣይም ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን መሰል ስራዎችን ለማቅረብ እንደሚያስቡ ተናግሯል።

አዘጋጅ ተክሌ ደስታ በበኩሉ የትያትር ዝግጅት ብዙ ልምምድን የሚጠይቅ ፈታኝ  ስራ መሆኑን በማንሳት ብዙ የሚደከምበትን ስራ ተደራሽነት ለማስፋት መንግሥት ለትያትር እድገት የበኩሉን ድጋፍ  ማድረግ አለበት ብሏል ። አያይዞም ባለሙያዎች እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን  ሚና በአግባቡ መወጣት ቢችሉ የሚል ሃሳብን አንስቷል ።

ከትያትሩ ታዳሚዎች አንዱ የሆነው የህግ ትምህርት ቤት 5ተኛ አመት ተማሪ በፍቃዱ ተክሉ እስካሁን  ባለው በዩንቨርሲቲ ቆይታው እንደዚህ አይነት ዝግጅት አለማየቱን በማንሳት ትያትሩ ቤተሰብን እንዲሁም  ሃገርን ማሳየት የሚችል አስተማሪ ትያትር ነው ብሏል። በመርሃግብሩ በመታደሙም ደስተኛ መሆኑን በመግለፅ ለቀጣይ ጊዜም እንደዚህ ያሉ አስተማሪ ትያትሮች መቅረብ ቢችሉ ሲል ጠይቋል ።

ተዋናይ ሱራፌል ተካ በበኩሉ ኪነጥበብ ቁምነገርን በቀልድ እያዋዛ ተማሪዎችን ብሎም ሃገርን የሚያንፅ ሁነኛ መሳሪያ መሆኑን አስረድቷል። ተማሪዎቹ የሰጡት አቀባበል ትያትሩ አስተማሪ መሆኑን የሚያረጋገጥ ነው በማለት በሰጡት መልካም ምላሽ እና አቀባበልም ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል ።

በመጨረሻም መርሃግብሩ  በተማሪዎች እና በኪነጥበብ ባለሙያዎቹ የጋራ ፎቶ በመነሳት ተቋጭቷል ።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et