የመንፈቅ ዓመት የወላጆች ቀን ተከበረ

በሀዩ የማ/ብ ሞዴል ትምህርት ቤት የመጀመርያውን መንፈቅ ዓመት የወላጆች ቀን አከበረ::

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ስራውን የጀመረው የማህበረሰብ ሞዴል ሁ/ደ/ት/ቤት የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የወላጆች ቀን በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ አክብሯል::

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስ/ል/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ ሲናገሩ ዩኒቨርሲቲው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ የሆነውን የትምህርት ስራ የልህቀት ማዕከል ሆኖ እያከናወነ እንደሚገኝና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተስተዋለውን የትምህርት ጥራት መዳከምና የውጤት ማሽቆልቆል ለማሻሻል በማሰብ የማህበረሰብ ሞዴል ት/ቤቱን ማቋቋሙን አስታውሰዋል። ም/ፕሬዚደንቱ አክለውም የትምርህት ስራ የብዙ ባለድርሻዎችን ትብብር የሚጠይቅ እንደመሆኑ ከተማሪ ወላጆችና ከት/ቤቱ ባለሙያዎች ጋር የሚደረገው ውይይት ለሚጠበቀው ውጤታማ ሥራ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የትምህርት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሳሙኤል አሰፋ በበኩላቸው ሞዴል ት/ቤቱ የመግቢያ ፈተናውን ያለፉና የመጀመሪያ መንፈቅ አመት ትምህርቱን ተከታትለው የጨረሱ 126 ተማሪዎችን ይዞ የሁለተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ የት/ት ዝግጅትና የካበተ የሙያ ልምድ ያላቸውን መምህራን በመመደብ ጥራት ያለውን ትምህርት እየሰጠ እንዳለ ገልፀዋል። ዲኑ ት/ቤቱን በመማሪያና መርጃ መፃሕፍት እንዲሁም በላይብረሪና የቤተ-ሙከራ አገልግሎት የተደራጀ ለማድረግ ጠንካራ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው  በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ውጤታማ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሆነ ገልፀዋል።

የሞዴል ት/ቤቱ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ማንደፍሮ የዕለቱ ፕሮግራም የተዘጋጀበትን ዋና አላማ ሲያስረዱ በሞዴል ት/ቤቱ የመጀመሪያ መንፈቅ የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን አጠቃላይ ውጤት ለወላጆች ለማሳወቅ እና ት/ቤቱ ያለበትን ደረጃ ለወላጆች ግልጽ ለማድረግ እንዲሁም ከተማሪ ወላጆች ደግሞ ገንቢ አስተያየትና የማሻሻያ ሀሳቦችን ለመሰብሰብ ታስቦ መሆኑን ገልጸዋል። ዳይሬክተሩ ዝርዝር የስራ ሪፖርት ካቀረቡ በኃላ የተማሪ ወላጆች ልጆቻቸው መልካም ዜጎችና ኃላፊነት መሸከም የሚችሉ ስኬታማ ሰዎች እንዲሆኑ ለማስቻል የሚረዳ አጭር ስልጠና በዩኒቨርሲቲው የሳይኮሎጂ ት/ክፍል መምህርና የስነ ልቦና አማካሪው ሃብተማርያም ካሳ ተሰጥቷቸዋል::

ትምህርት ቤቱ በሰጠው ምዘና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት የዕለቱ ተሸላሚዎች በሶስት ደረጃዎች ማለትም እጅግ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ (ከ90% በላይ)፣ በጣም ከፍተኛ (ከ85% በላይ)፣ ከፍተኛ ውጤት (ከ70% በላይ)፣ ያስመዘገቡ ተብለው የተለዩ ሲሆን በጠቅላላው ከ80 በላይ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በዕለቱ ከተማሪ ወላጆች የተለያዩ ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተው ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኃላ ለተሸላሚ ተማሪዎች፣ መምህራን እና ወላጆች እውቅና የመስጠት ስነስርዓት ተከናውኗል::

ከሴት ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ተሸላሚ የሆነችው ተማሪ ተወዳጅ ደግፌ የትምህርት ቤቱ መምህራንና ሰራተኞች ተማሪዎችን በሚፈልጉበት አቅጣጫ ሁሉ እያገዙ እንደሚገኙ ጠቅሳ ምስጋና ያቀረበች ሲሆን ፕሮግራሙን የታደሙ የተማሪ ወላጆችም ውይይቱን እጅግ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። በፕሮግራሙ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች ተሳትፈዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et